የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት እየተከናወኑ ናቸው፦ የተከበሩ አቶ መቱ አኩ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ብሔረሰቦች ምክር ቤት 3ኛ ዙር 4ኛ መደበኛ ጉባኤውን በቴፒ ከተማ ማካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የምክር ቤቱ የተከበሩ ዋና አፈ-ጉባኤ አቶ መቱ አኩ ጉባኤው ያለፉትን የ9 ወራት አፈፃፀም በመገምገም ለቀጣይ በቂ ግብአት የሚወሰድበት መሆኑን ገልፀው ምክር ቤቱ ህገ መንግሥታዊ ተልዕኮውን አንግቦ የክልሉን ህዝብ መብትና ጥቅም በማስከበር ረገድ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡

ምክርቤቱ በህገ መንግሥትና ፌዴራልዝም አስተምህሮ ላይ መሠረት በማድረግ የብሔረሰቦችን መብት ከማስከበር አንፃር በክልሉ ካሉ ሁሉም መዋቅሮች ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑን ዋና አፈ ጉባኤው አንስተዋል።

ከዚህም ባሸገር ምክር ቤቱ የተለያዩ ክልላዊና ሀገራዊ ኩነቶች በስኬት እንዲጠናቀቁ ብርቱ ጥራት ሲያደርግ መቆየቱን የተናገሩት የተከበሩ አቶ መቱ የክልሉ ህዝቦች በክልሉና በፌዴራል ህገመንግስት ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲይዙ መድረኮች በመፍጠር የተለያዩ ውይይቶችን ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል፡፡

የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ታሳቢ ያደረጉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው ያሉት የተከበሩ አፈ ጉባኤው የምክር ቤቱ አባላት የብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

የክልሉ ብሔረሰቦች ምክርቤት የ2017 በጀት ዓመት የ9 ወራት አፈጻጸም ሪፖርት በምክር ቤቱ ምክትል አፈጉባኤ በተከበሩ አቶ መሰለ ከበደ እየቀረበ ይገኛል።

በጉባኤው የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ አቶ ፍቅሬ አማን፣ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ፣ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ቆጭቶ ገብረማርያም ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

በተከተል ወ/ሚካኤል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *