





የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ትምህርት ቢሮ የ2017 ዓ.ም የስራ እና ቴክኒክ ትምህርት በኮንታ ዞን ጪዳ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት አስጀመሯል።
በክልሉ በ2017 ትምህርት ዘመን ከ16 ሺህ በላይ ተማሪዎች በሙያ ለመማር መመዝገባቸው ታውቋል።
በማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ላይ የተገኙት የክልሉ ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊና የስርዓተ-ትምህርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አባቴ ኡቃ በሀገራችን ያለውን የትምህርት ስብራት ለመጠገን በተጠናው አዲሱ ፍኖተ ካርታ ውስጥ ይህ የስራና ሙያ ትምህርት ተካቶ በሀገሪቱ በ8 ትትምህርት ሙያ መስኮች መጀመሩን አንስተዋል።
በክልል ደረጃ በ12 ሙያ መስኮች በ182 2ኛ ደ/ት/ቤቶች የሚገኙ 16,399 ተማሪዎች ሙያ መርጠው እንዲማሩ ለማድረግ በዛሬው ዕለት መርሀ ግብሩን ማስጀመራቸውን ያብራሩት አቶ አባቴ ተማሪዎች ከቀለም ትምህርት ባሻገር በቂ ሙያ ቀስመው ስራ ፈጣሪ እንዲሆኑ፣ በሙያ ተቀጥረው እንዲሰሩና በዘርፉ ክህሎት እንዲጨብጡ ለማስቻል መሆኑን በመግለፅ በዋናነትም የወጣቱን ስራ አጥነት ለመቅረፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው ብለዋል።
በኮንታ ዞን ደረጃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀማመሩ አበረታች የትምህርት ንቅናቄ ስራዎች ተጠናክረው ሊመሩ እንደሚገባ ያነሱት የቢሮ ም/ኃላፊው ለትምህርት ስራ ውጤታማነትና ለመርሀ-ግብሩ ስኬት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አስገንዝበዋል።
የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪና ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ወጁ እንደመንግስት በትምህርት ዘርፍ ያሉ ጉድለቶችን ለመቅረፍ ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቁመው ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን ተማሪዎች በሙያ እንዲጎለብቱ የተጀመረው ስራ ስራ አጥነት ለመቅረፍና ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን ለመፍጠር ትልቅ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አጥናፉ አበራ ከቀለም ትምህርት በተጨማሪ የሚሰጠው የስራና ሙያ ትምህርት በዞኑ የተጀመረውን የትምህርት ስራ በበለጠ በማሻሻል ለሀገር ዕድገት ድርሻቸው የሚወጡ ዜጎችን ለመፍጠር እንደሚያግዝ አስረድተው በዞኑ በ7 2ኛ ደ/ት/ቤቶች 710 ተማሪዎች በ9 ሙያ መስኮች እንዲሰለጥኑ መለየቱን አብራርተዋል።
በመርሀ-ግብሩ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ም/ኃላፊና የስርዐተ-ትምህርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አባተ ኡቃ፣ የዞኑ ም/አስተዳዳሪና ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ወንድማገኝ ወጁ፣ የጪዳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ዓለሙ ኮቾ፣ የዞኑ ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አጥናፉ አበራ፣ የክልልና የዞን ትምህርት ቢሮ አመራሮችና ባለሙያዎች፣ መምህራን፣ ተማሪዎችና ሌሎች ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን የሙያ ማሰልጠኛ ክፍሎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
