አንደኛው የአትሌቲክስ ውድድርና 4ኛው የባህል ስፖርቶችና ፌስቲቫል በኮንታ ዞን አመያ ከተማ ተጀመረ

Spread the love

በዚሁ የውድድር መክፈቻ ፕሮግራም ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የኮንታ ዞን ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ ደምሴ ዜጎች በባህል ስፖርት ውድድሮች መሳተፋቸው የርስ በርስ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ሚናው የላቀ ነው ብለዋል።

የክልሉ ባህል ስፖርቶች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አፈወርቅ ዳና ባስተላለፉት መልዕክትም ባህል ስፖርቶችና ፌስቲቫሎች የክልሉ ህዝብ የርስ በርስ ግንኙነትን ከማጠናከርም ባለፈ ቱባ ባህሎችን በአደባባይ ለማስተዋወቅ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ አካሉ በልሁ የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድር ሀገራችንን በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ብላ እንድትደምቅ ያደረገ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል ።

ሀገራችን ስሟ በአትሌቲክስ ስፖርት ገኖ እንዲወጣ ካደረጉት ክልሎች ውስጥ አንዱ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

ክልላዊ ህብረብሔራዊነት ለማጠናከርም ስፖርት ያለው አቅም ትልቅ ነው ብለዋል ።

የኮንታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታከለ ተስፉም በፕሮግራሙ ላይ በመገኘት ስፖርት የአካባቢውን ህዝብ የርሰ በርስ ግንኙነት የሚያጠናክርና የህብረብሔራዊነት ማሳያ ነው ብለዋል።

የባህል ስፖርቶች ወደ ውድድር ደረጃ ማደጋቸው ባህሎቻችንን በአደባባይ በማስተዋወቅ ወንድማማችነትን ይበልጥ ለማጠናከር ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል።

የክልሉ ባህል ስፖርትና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ብላቴ ባስተላለፉት መልዕክት በተለያዩ የባህልና አትሌቲክስ ስፖርቶች ውድድር አሸናፊው የክልሉ ህዝብ ነው ብለዋል

የባህል ስፖርቶች ባላቸው ትልቅ እሴትም ለክልሉ ህዝብ አንድነትና ሰላም መሰረት ናቸው ሲሉም አቶ ፋንታሁን ተናግረዋል ።

የባህል ስፖርቶች ሳይበረዙና ሳይጠፉ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ጠቀሜታቸውን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል ።

የአትሌቲክስ ስፖርት ውድድር ለበርካታ ታዳጊ ወጣቶች ተስፋ የሀገራችን ሰንደቅዓላማ ከፍ ብሎ በዓለም ደረጃ እንዲውለበለብ ትልቅ አቅም ያለው ነው ብለዋል።

በክልሉ ሁሉም ዞኖች የአትሌቲክስ ስፖርትና የባህል ስፖርት ውጤታማ እንዲሆኑ የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ትኩረት አድርጎ ይሰራል ብለዋል።

የየዞን ልዑኩ የባህል ፌስቲቫል ትርዒት በማሳየት ለውድድሩ ድምቀት ፈጥረዋል።

በተከታታይ 4ቀናት በሚኖረው ውድድር የማርሻል አርት ትርዒት ፣ የሚዛን አትሌቲክስ ማዕከልና የአየሁ አትሌቲክስ ማዕከል ተሳታፊዎች ናቸው።

አንደኛውየአትሌቲክስ ስፖርት እና 4ኛው የባህል ስፖርትና ባህላዊ ፌስቲቫል በ5000 ሜትር የወንዶች ፍጻሜ እንዲሁም በኮርቦ ውድድር ተጀምሯል።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *