ለጋራ ብልፅግና የተጋመደውን ውጥናችንን በጋራ ቃል ኪዳናችን እያፀናን የብልፅግና ጉዟችንን ማፋጠናችንን እንቀጥላለን – አቶ አደም ፋራህ

Spread the love

ለጋራ ብልፅግና የተጋመደውን ውጥናችንን በጋራ ቃል ኪዳናችን እያፀናን የብልፅግና ጉዟችንን ማፋጠናችንን እንቀጥላለን ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንትና በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ።

አቶ አደም ፋራህ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ለ19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም እንኳን ኢትዮጵያዊያን በመገናኘት ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን እና ታሪካቸውን መተዋወቅና መማማር በሚያስችል መልኩ በሚገልፁበት እንዲሁም ትስስራቸውንና ህብረብሔራዊ አንድነታቸውን በማጠናከር የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን ለማድረግ ቃል ኪዳናቸውን በሚያድሱበት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን አደረሳችሁ፣ አደረሰን ብለዋል።

የዘንድሮውን በዓል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በውቢቷ የፍቅር ከተማ አርባምንጭ በድምቀት ኢትዮጵያዊነት ከፍ ብሎ አክብረናል ሲሉም ገልጸዋል።

የብዝሃ ማንነት ሀገር መሆኗን ማመንና ማስተናገድ መፃኢ የጋራ ዕጣ ፈንታችን ያመረ እንዲሆን ያስችላልና ከስሜትና ጠርዝ ከረገጠ አዝማሚያ ታቅበን ልዩነቶቻችንን አክብረን አንድነታችንን አጠናክረን ከሁላችን ለሁላችን የሆነች ኢትዮጵያን እናፀናለን ብለዋል።

ለጋራ ብልፅግና የተጋመደው ውጥናችን፣ በጋራ ቃል ኪዳናችን እያፀናን፣ እኩልነት እና አንድነትን በፅኑ መሰረት ላይ በመገንባት እኛ የኢትዮጵያ ልጆች የብልፅግና ጉዟችንን ማፋጠኑን እንቀጥላለን ሲሉም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያዊያነት ይለመልማል፣ ኢትዮጵያ ትበለጽጋለች ብለዋል አቶ አደም በመልዕክታቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *