በ2016 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ከ170 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ለግል ሴክተሮችና ለባንኮች መሰጠቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ÷ በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራት ረዘም ላለ ጊዜ የቆየ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖ፣ ዓለም አቀፋዊ ግጭቶች፣ የውስጥ ችግሮች እና የውጭ ጫናዎች በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ጫና ማሳደሩንም አብራርተዋል፡፡
በእነዚህ ድምር ምክንያቶች የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራትን መጠገን አልቻልንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ የማክሮ ፋይናንሻል መዛባትን በሚመለከት የተሠራው ፊፎርም በብዙ ማሳያ ከፍተኛ መሻሻሎች ታይቶበታል ብለዋል፡፡
የብር ኖት ከመቀየር ጀምሮ ሲሠራ የነበረው ሪፎርም በተወሰነ ደረጃ መሻሻል እንዲታይ ማድረጉን ጠቅሰው÷ በቀጣይ መታየት ያለባቸውና ቀሪ ሥራ የሚፈልጉ ጉዳዮች እንዳሉም አመላክተዋል፡፡
የፊሲካል ፖሊሲ አቅጣጫዎችና ሥራዎች አሁን ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥሉት መንግሥታትም ጭምር ፋይዳ ሊያመጡ የሚችሉ ስብራቶች ተጠግነውበታል ነው ያሉት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ላይ እንደጠቀሱት፤ በአማራ ክልል ባለፉት አምስት አመታት የዓባይ ድልድይን ጨምሮ የክልሉን ልማት ለማፋጠን የሚረዱ በርካታ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡
ለዚህም በክልሉ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታ ስራ የተጀመረ ሲሆን ፥ ከዚህም ውስጥ 1 ሺህ 300 ኪሎ ሜትር ያህሉ ተጠናቆ ስራ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡
አዲሱ የዓባይ ድልድይ በአማካይ 50 ሜትር ስፋት ያለው በሁለት ረድፍ በእያንዳንዳቸው ሶስት መኪና የሚያሳልፍ፣ ሰፊ የሳይክልና የእግረኛ ቦታ ያለው መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ይህም በኢትዮጵያ በከፍተኛ ወጪና ጥራት የተሰራ የመጀመሪያው ድልድይ ያደርገዋል ብለዋል፡፡
ለፕሮጀክቱም 2 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገደማ ወጪ መደረጉን ነው የገለጹት፡፡
ፕሮጀክቱ በጥራት በአስፓልት ኮንክሪት የተሰራ መሆኑንና በጥንቃቄ ከትውልድ ወደ ትውልድ መተላለፍ በሚችል መልኩ መገንባቱንም አንስተዋል፡፡
