በክልሉ ሠላምና ፀጥታን ለማረጋገጥ የፀጥታ መዋቅሮች ተቀናጅተው በሰሩት ስራ ዘርፈ ብዙ ውጤቶች ተመዝግቧል:-ኮሚሽነር ሰብሰቤ ሻዎኖ

Spread the love

የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የ2015 ዓ.ም የዕቅድ አፈፃፀምና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በታርጫ ከተማ እየመከረ ይገኛል ።

በመድረኩ ኮሚሽነር ሰብሰቤ ሻዎኖ እንደተናገሩት በ2015 በጀት ዓመት በክልሉ በምዕራብ ኦሞ ዞን በሱሪ ፣ በቤሮና በጎርጌሻ ወረዳዎች፣በቤንች ሸኮ ዞን በጉራፈርዳ ፣ በደቡብ ቤንችና በሸኮ ወረዳዎች የነበሩ የፀጥታ ችግሮችን ህብረተሰቡን በማሳተፍ በተሰራው ስራ ውጤቶች ተመዝግቧል ብለዋል።

በሌላ በኩልም በሸካ ዞን ቴፒ ከተማና የኪ ወረዳ ሲስተዋል የነበረው የፀጥታ ችግሮች በአካባቢው በተቋቋመው ሰላም አፈላላጊ ኮሚቴ ጋር በተሰራው ስራ የተጎጅ ቤተሰቦች ጋር እርቀ-ሠላም እንዲወርድና አንፃራዊ ሠላም ወደ ዘላቂ እንዲሸጋገር መደረጉንም ኮሚሽነር ሰብሰቤ ሻዎኖ አብራርተዋል ።

በመደበኛ የፖሊስ ተግባራት ላይ በማተኮር የመከላከልና የምርመራ ስራው ላይ ከክልል እስከ ወረዳ ባሉት ጥምር የፀጥታ ሀይሎች የጋራ ርብርብ በርካታ ውጤቶች የተመዘገቡትን ያህል በየዘርፉና በየደረጃው አሁንም ያልተሻገርናቸው በርካታ ጉዳዮች በቀጣይም ትኩረት የሚሹ ናቸውም ብለዋል።

የትራፊክ አደጋ መከላከልና ቁጥጥር ስራው አሁንም ትኩረት የሚፈልግ ጉዳይ በመሆኑ የጋራ ርብርብ እንደሚጠይቅ ገልፀዋል ።በትራፊክ አደጋ መከላከል ስልጠና ያልወሰዱ አካላትን ለማስልጠን ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ያነሱት ኮሚሽነሩ በምርመራ የሚሳተፉ አካላትም የሚሰለጥኑ መሆናቸውም ተገልጿል ።

የማዕረግ ዕድገት ጊዜ ቆይታን የሸፈኑ ስልጠና ወስደው የማዕረግ ዕድገት ማግኘት የሚገባቸው የፖሊስ አባላት መኖራቸውን ያነሱት ኮሚሽነር ሰብስቤ እነዚህ በቅርብ ቀን ወደ ስልጠና የሚገቡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

የክልሉ ሠላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ በመድረኩ ተገኝተው እንደተናገሩት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ከሌሎች ፀጥታ መዋቅሮችና ባለድርሻ አካላት ጋራ በመሆን በሰሩት ጠንካራ ስራ ክልላችን አሁን የተሻለ ሠላም ላይ መድረሱን ተናግሯል ።

የክልሉ መንግስትና በየደረጃው ያሉት አካላት ከትናንት በተሻለ ሁኔታ በክልላችን ዘላቂ ሠላምና ፀጥታ እንዲሰፍን ሁሉም በጋራ መስራት እንደሚገባ አቶ አንድነት ጠይቀዋል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *