

ኢትዮጵያ የተለያዩ አገር በቀል ዕዉቀት ባለቤት ናት።ይህንን ለሁለንተናዊ እድገት መጠቀም ያስፈልጋል። በግብርና ሲታይ ዘመናዊ ግብርና ከአገር በቀል ዕዉቀት ጋር በማጣመር የመስራቱ ልምምድ እያደገ ነዉ።
በሀገራችን በተለያዩ ሥፍራዎች ለምግብነት ቢያገለግልም በአብዛኛው አካባቢዎች እንደ አረም የሚታየው በሳይንሳዊ ስሙ አማራንተስ (ካቲላ) የሚባለው ሰብል በስፋት እንደ ምግብ ይጠቀሙ ዘንድ የተለያዩ ጥረቶች ቢጀምርም አጥጋቢ ውጤት አልታየበትም። ካሉ በርካታ የምግብ ዓይነቶች አንዱ ያልታወቀ እና እየጠፋ የሚገኘው (ካቲላ) አማራንተስ ነዉ።
ካትላ አገርን ብቻ ሳይሆን አፍሪካን ሊለወጥ ይችላል። የምግብ እጥረት የሚሸፈን ፣የሕፃናትን እድገት የሚያግዝ፣ ከተዘራ ቶሎ ደርሶ የምግብ እጥረትን የሚቀንስ እንደሆነ ይታመናል። ይህ ደግሞ በዉጭ አገሮች በከፍተኛ ዋጋ የሚሸጥ ዉድ ምግብ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ።
ካቲላ ምግብ ብቻ ሳይሆን መድኃኒትም ነው። ክብደት ለመቀነስ፣ ለአጥንት ጤና ችግር፣ የደም ማነስ፣ ልብን ለማጠናከር፣ ለካንሰር በሽታ፣ በሽታን ለመከላከልና አቅምን ለማሻሻል፣ የስኳር በሽታን ለመቋቋም፣ ለቆዳ ጤና ችግር፣ የፀጉር ጤና ችግር እንዲሁም ሌሎች በርካታ ጥቅሞችና መድኃኒት እንደሆነ በርካታ ጥናቶች ያረጋግጣሉ።
ሰብሉ በኢትዮጵያ እያለ በስፋት ባለመታወቁና ከምግብ ዝርዝር ዉስጥ ገብቶ በፓኬጅ ባለመዘጋጀቱ እናቶች እና ህፃናት በተመጣጣነ የምግብ እጥረት ሳቢያ ይጎዳሉ።
ኬንያ አሁን በእርሻ ሥርዓት ዉስጥ አስገብተው፣ በካቲላ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን የሚያመርቱ 6 ፋብሪካዎች ከፍታ ለአገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይሆን ለዉጭም ሀገር ገበያም ጭምር እያቀረበች ትገኛለች።
ታዲያ ይህ የተመጣጠነ የምግብ ይዘት ያለው ካቲላ በእርሻ ሥርዓት ገብቶ ህብረተሰቡ የምግብ ፍላጎት ብቻ ሳይሆን በቀን የሚፈለገውን የተመጣጠነ የምግብ ይዘት እንድያገኝ ትኩረት ተሰጥቶ መሰረት አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ወሳኝ መሆኑ ታምኖበታል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በምዕራብ ኦሞ ዞን አካባቢዎች ካቲላ በብዛት እንደሚመረትና በተለይም በዞኑ ከሚገኙ ብሔረሰቦች የመኤኒት ብሔረሰብ ካቲላ በቀላሉ የሚያመርት፤ በትንሽ ቦታ ብዙ ምርት የሚያገኝ፣ ከምግብነት ባለፈም ለመድኃኒትነት እንደሚጠቀም እና ሦስት ዓይነት የካቲላ ዝርያ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ኃላፊ አቶ መልኬ ኬላጌ ይናገራሉ።
ሆኖም ግን ሰብሉ አሁን በዞኑ በአብዘኛዎች ቦታዎች እየተመነመነ እንደሚገኝ ገልጸው በምግብ ራስን ለመቻልም ሆነ በመድኃንነት በማገልገል የራሱ ሚና በመኖሩ ለዚህም ላለፉት ሰባት ዓመታት በዞኑ በዚህ ከቲላ ሰብል ላይ በርካታ ጥናቶች ተደርጎ የተረጋገጠ መሆኑን አንስተዋል ።
የምዕራብ ኦሞ ዞን ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃ እና ህብረት ስራ መምሪያ እንደሀገርና ክልል ትኩረት ያልተሰጠው እንዲሁም እየተመነመነ የመጠውን ካቲላ ሰብል በብዛት በማልማትና ዝሪያው እንዳይጠፉ በመጠበቅ እንዲሁም ማህበረሰቡ የካቲላ ሰብል ምርት ተጠቃሚ ለማድረግና ሰብሉን ምርት ወደሌሎች አካባቢ እንዲሰፋ ለማስቻል ሰፊ ስራ እያከናወነ ይገኛል።
ካቲላ ለምነት ባለበት ሥፍራ ከፍተኛ ምርት ቢሰጥም በየትኛው የአፈር ዓይነት ይበቅላል ያሉት አቶ መልኬ ይህ ደግሞ በዘመናዊ መልክ ቢሠራበት ደግሞ የበለጠ ምርት እና ምርታማነት እንደምጨምና ለዉጭም ገበያ መላክ እንደምንችል አመላክተዋል፡፡
ካቲላ ደግሞ ከየትኛውም ሰብልና አትክልቶችን በተሻለ የተመጣጠነ ምግብ ይዘት እና ከፍተኛ የሆነ የዘይት መጠን በውስጡ እንደሚይዝ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስተር ለሁለት ዓመታት በካሄደው ጥናት ማረጋገጡን ኃላፊው አክለውም ገልፀዋል፡፡
በምዕራብ ኦሞ ዞን በመኤኒት ብሄረሰብ በብሔረሰቡ ”ካቲላ” የሚል ስያሜ የተሰጠውና በሳይንሳዊ መጠሪያው ደግሞ ”አማረንተስ” የተሰኘው ይኸው ተክል በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎችም ተክሉ የሚታወቅ ቢሆንም በመኤኒት ብሔረሰብ ዘንድ ልዩ ቦታ የሚሰጠውና ከብሔረሰቡ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ባህላዊ ምግባቸው በዘመናዊ መንገድ ለማልማት የሚያስችል ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በዓመት ሁለት በመኸርና በበልግ ወቅት የሚመረት በመሆኑ እንደዞን ካቲላ ሰብል ምርት ለመስፋፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንዲያስችል በዘንድሮው በ2016 በጀት ዓመት በበልግ እርሻ ወቅት 1250 ሄክታር መሬት በካቲላ ሰብል ለመሸፈን እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ መልኬ ተናግረዋል ፡፡
በብሄረሰቡ ዘንድ ተወዳጅ የሆነው ካቲላ በምዕራብ ኦሞ ዞንና ብሄረሰቡ በሚገኙባቸዉ አካባቢዎች እንደሚመረት ጠቅሰዋል ኃላፊው፡፡
ከኢኮኖሚ ጠቃሜታው አንፃር ከሰልጥ ቀጥሎ ካቲላ በሁለተኛ ደረጀ ላይ የሚቀመጥ መሆኑን ያብራሩት አቶ መልኬ ኬላጌ የምርት መጠኑን በማሻሻል ውጤታማ ለመሆን የክልሉ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ በበጀት በመደገፍ እና ዞኑም ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከቻለ ከክልሉ አልፎ ለሀገር ሊሆን የሚችል መሆኑን አንስተዋል።
አርሶ አደሮቹም ቢሆኑ የካቲላ ሰብል ምርት በዞኑ የሚመረትና የሚመገብ ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎች አካባቢ ማስፋት ከተቻለ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉበት በመሆኑ ትኩረት አድርገው መስራት እንደለባቸው መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።
