የክልሉ ህዝብ የብዘሃ  ባህል ባለቤት መሆኑ አንዱ የቱሪዝም ፀጋ ነው።

Spread the love

ቱርዝም ለክልሉ ትልቅ የኢኮኖሚ አቅም በመሆኑ በልዩ ትኩረት እየተሰራ ነው በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የቱሪዝም ፀጋዎች ዘርፈ ብዙ ናቸው። የክልሉ ህዝብ የብዘሃ  ባህል ባለቤት መሆኑ አንዱ የቱሪዝም ፀጋ ነው።

ክልሉ የበርካታ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መኖሪያ በመሆኑ ብዘሃ ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ቅርስ፣ የአኗኗር  ዘዬ እና የመሳሰሉት ህብረ-ብሔራዊ ውበትን የሚያጎሉና የቱሪዝም ሀብት የሚሆኑ ዕሴቶችና ትውፊቶች መናኸሪያ ነው። በተጨማሪም ክልሉ በተፈጥሮ ፀጋ የታደለ ከመሆኑም ባሻገር የክልሉ ህዝቦች ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ፣ ተሰናስኖና ተቻችሎ የመኖር የረጂም ጊዜ ልምድና ልዩ ጥበብ ያላቸው በመሆኑ በርካታ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ የቱርስት መዳረሻዎችን አቅፎ የያዘ ነው፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ባህል፣ ቱርዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ  አቶ ፋንታሁን ብላቴ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ የባህል አቅሞች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ  መሆኑን ገልፀው በዚህም በርካታ የሀገራችን ሚዲያዎች የክልላችን ህዝቦች ባህል፣ ቅርስ፣ ታሪክና  ትውፊታዊ ዕሴቶችን እንዲሁም ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ መስህቦችን በተለያዩ መንገዶች እያስተዋወቁ ይገኛሉ ብለዋል። ዚህም የክልሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ጎብኝዎች እንዲጎበኝ በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የክልላችን የቱሪዝም አቅሞች ከማጎልበት አንፃር በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ  አነሳሽነት እና ሀሳብ አመንጪነት የተሰሩ  የኮይሻ  ገበታ ለሀገር አካል የሆኑት የሀላላ ኬላና የጨበራ ዳና ሎጂ  እንዲሁም የገበታ ለትውልድ አንዱ አካል የሆነው በደንቢ ሰው ሰራሽ ግድብ አካባቢ የሚሠራው የደንቢ ሎጅ ተጠቃሽ መሆናቸውን አቶ ፋንታሁን አብራርተዋል።

በክልላችን የሚገኘው ገበታ ለሀገር የኮይሻ ፕሮጀክት ሁለት ትላልቅ ክላስተሮችን አስተሳስሯል፡፡ ከነዚህም አንዱ የሀላላ ቅልንጡ ሎጂ ሲሆን ይህም ክልላችን ብሎም ሀገራችን በምስራቅ አፍሪካ ላይ በቱርዝም መዳረሻነት ከፍተኛ አቅም እንደላት በተጨባጭ ያሳየና የክልላችን ገጽታ በጥሩ ሁኔታ የገነባ ታላቅ የቱሪዝም መዳረሻ ነው ብለዋል ኃላፊው፡፡

ጊቤ 3 ግድብ ላይ በተፈጠረው ሀይቅ ላይ በርካታ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ተደራጅተው ገቢ እንዲያገኙና የኢኮኖሚ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ በማሰብ ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ውጤታማ ስራ እየሰራ መሆኑን አቶ ፋንታሁን ገልጸዋል።

በክልላችን በቤንች ሸኮ ዞን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ መሠረተ ድንጋይ ተቀምጦለት ወደ ግንባታ ስራ የተገባው በደንቢ ሰው ሰራሽ ሀይቅ ላይ የሚሰራው ገበታ ለትውልድ አንዱ አካል የሆነው የደንቢ ሎጅ  ሌለኛው የክልሉን የቱሪዝም አቅም የሚያነቃቃ ፕሮጀክት ነው ብለዋል አቶ ፋንታሁን።

የፌዴራል መንግሥት በክልላችን የቱሪዝም ዘርፉን ለማነቃቃት የጀመራቸው ፕሮጀክቶች በቀጣይ የግል ባለሀብቱ በዚህ ዘርፍ ተሰማርቶ ማልማት እንዲችልና ሰፊውን የቱሪዝም ፀጋዎች አሟጦ እንዲያወጣ በር ካፋች ታላቅ መደላድል የፈጠረ እንደሆነ ያብራሩት ኃላፊው ይህንን ተከትሎ ሁሉም ዞኖች በየዞኑ ያሉትን መስህቦች ተደራሽ ማድረግ እንዲችሉ በመሠረተ ልማት እንዲተሳሰሩ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንዳለ ገልፀዋል፡፡

በክልሉ የባህል መንደር ለመገንባት ዕቅድ መያዙን የጠቀሱት አቶ ፈንታሁን ይህም ሲሳካ የክልሉን ህዝብ ቱባ ባህሎችን፣ ቅርሶችንና ትውፊታዊ ዕሴቶችን አጎልቶ በሚያሳይ መልኩ የሚደራጅ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም የክልሉን የቱሪዝም አቅም የተሻለ ደረጃ ላይ በማድረስ የገቢ ምንጭ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት ሁሉም የባለድርሻ አካላት ደግፈው ለውጤት እንዲያበቁ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *