መንግሥት ለዜጎች ሕይወት መሻሻል የቀረጻቸው ፕሮግራሞች በውጤት ሊመሩ ይገባል- ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መንግሥት ለዜጎች ሕይወት መሻሻልና ለተመጣጠነ ሥርዓተ ምግብ መረጋገጥ የቀረጻቸው ፕሮግራሞች፣ ውጤት ተኮር በሆነ መንገድ ሊመሩና ሊተገበሩ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንን የገለጹት፣ የክልሉ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ማስተባበሪያ ዩኒት የሰቆጣ ቃል ኪዳን ሥራዎችንና የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት አፈጻጸምን በገመገሙበት ወቅት ነው። በመድረኩ ላይ እንደተጠቀሰው፣ መንግሥት ለዜጎች ማኅበራዊ ዋስትናና ጤና ትልቅ በጀት መድቦ የሚንቀሳቀስባቸው ፕሮጀክቶች በተገቢዉ ተመርተዉ ውጤት ሊያመጡ ይገባል።

በክልሉ ሕፃናት ላይ የሚታየውን የመቀንጨር ችግር ለመቅረፍና የተመጣጠነ ሥርዓተ ምግብን ለማስፈን እየተከናወነ ያለው የሰቆጣ ቃል ኪዳን ሥራ፣ የክትትል ክፍተት እንዳይገጥመው አቅጣጫ ተቀምጧል።

ርዕሰ መስተዳድሩ እንደገለጹት፣ የሥርዓተ ምግብ ምክር ቤት (Nutrition Council) እስከ ቀበሌ ድረስ በቴክኒክ ኮሚቴ ተደራጅቶ የአፈጻጸም ክትትል ሊያደርግ ይገባል።

ከፋይናንስ አጠቃቀም ጋር በተያያዘም፣ የ2018 በጀት ዓመት የሰቆጣ ቃል ኪዳን “ማቺንግ ፈንድ” ያለበት ደረጃ ተለይቶ እንዲታወቅና የበጀት በጀት ዓመቱ የክልል፣ የዞንና የወረዳ ድርሻ በግልጽ እንዲቀመጥ አሳስበዋል። በተጨማሪም፣ የምግብና ሥርዓተ ምግብ ዩኒት በጽሕፈት ቤት ደረጃ ተደራጅቶ ሥራውን በባለቤትነት እንዲመራ መመሪያ ሰጥተዋል።

በክልሉ አበረታች ውጤት እየታየበት ነው የተባለው የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት፣ ይበልጥ ተደራሽ እንዲሆን ጥሪ ቀርቧል። በተለይም፦የአገልግሎት ተጠቃሚዎችን ቁጥር ማሳደግ፤የአገልግሎት አሰጣጥ ቅልጥፍናን ማረጋገጥ፤የከፋዮችን የደረጃ ሽግግርና የኦዲት ሥራዎችን አቀናጅቶ መምራት በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸው ተመላክቷል።

ቀሪ ዞኖች የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት ድጎማ በጀት አፈጻጸምን በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት አጠናቀው ለዜጎች የተሻለ የጤና ዋስትና እንዲሰጡ ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።

በአሻግሬ ገ/ወልድ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *