ቡናን በቴክኖሎጂ በማዘመንና ጥራቱን ጠብቆ ለዓለም ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ፦ ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ሸካ ዞን የዘመናዊ ቡና ልማት ኢንሼቲቭ ማስጀመሪያና ባለድርሻ አካላት ግንዛቤ ማስጨበጫ ንቅናቄ መድረክ በቴፒ ከተማ ተካሂዷል ።

በመድረኩ በቴፒ ግሪን ኮፊ ስቴት በ 4 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የሚጀመረዉ በጠብታ መስኖ እርሻ የሚለማዉ የቡና ኢንቨስትመንት የተመለከተ ማብራሪያ ቀርቦ ዉይይት ተደርጎበታል።

መንግስት መሰል የልማት ፕሮጀክቶች እውን እንዲሆኑ ላሳየው ቁርጠኝነትና ለከፈለው መስዋዕትነት ላቅ ያለ ምስጋና ያቀረቡት መድረኩ የተገኙ ተሳታፊዎች ናቸው ።

ነባሩን አሰራር በመተካት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ የቡና ልማት ኢንሼቲቭ መጀመሩ ለዘርፉ አዲስ ተስፋ የፈነጠቀ መሆኑንም ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

​ ሀገራዊ ዕድገቱን ለማፋጠን የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማሳካት በማንኛውም ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

​የአካባቢውን ማህበረሰብ ለመደገፍ ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉ ባለሀብቶችን ያመሰገኑ ሲሆን ይህ ፕሮጀክት ሳይዘገይ ፈጥኖ ወደ ተግባር እንዲገባና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ስራ እንዲሰራ ጠይቀዋል።

በመድረኩ ከተሳታፊዎች ለተነሱት አስተያየቶችና ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር)፣ ቀደም ሲል በሸካ ዞን ይስተዋል የነበረው የፀጥታ ችግር ለልማት ፕሮጀክቶች መስተጓጎል ዋነኛ ምክንያት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ሆኖም መንግስት ከህዝቡ ጋር በመቀናጀት ባከናወነው ስራ በአሁኑ ወቅት አስተማማኝ ሰላም ማስፈን መቻሉን ገልጸው፤አሁን ያለውን ሰላም ዘላቂ በማድረግ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በታቀደላቸው የጊዜ ሰሌዳ ለማጠናቀቅ በትኩረት ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል ።

​ቡናን በዘመናዊ መንገድ ማልማትና ቴክኖሎጂን መጠቀም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የክልሉን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ ብቸኛው አማራጭ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

በየደረጃው ያሉ አመራሮች ከህዝቡ ጋር ተቀራርበው በመወያየት የፕሮጀክቱን ፋይዳ ማስረዳት እንዳለባቸው የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ህዝቡ የልማቱ ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን ዋና ባለቤት መሆኑን ተገንዝቦ በንቃት እንዲሳተፍና እንዲደገፍ ጥሪ አቅርበዋል ።

ዘመናዊ አሰራርን በመከተል የቡናን ጥራት በማስጠበቅ ረገድ ፕሮጀክቱ የላቀ ሚና እንደሚጫወትና ይህም ክልሉ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ እንደሚያስችል መሆኑን የገለፁት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው ናቸው።

ይህ ፕሮጀክት የመንግስትና የህዝብ የጋራ ሀብት መሆኑን በመጠቆም፣ በዘርፉ ለዓመታት ሲስተዋሉ የቆዩ ማነቆዎችን ለመፍታት ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የሸካ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ በበኩላቸው ፤ ዞኑ ለዘመናት ቡና አምራች ቢሆንም፣ በአሰራርና በቴክኖሎጂ ክፍተቶች ምክንያት ማህበረሰቡ እስካሁን የሚገባውን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆነ ገልጸው ይህ ፕሮጀክት እነዚህን መሰረታዊ ችግሮች በዘላቂነት እንደሚፈታ ተናግረዋል።

​ያለንን ተፈጥሯዊ ፀጋ በመጠቀም ብልጽግናችንን የምናረጋግጥበት ታላቅ ዕድል ነው ያሉት የመንግስት ተጠሪው፤ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የዞኑ ማህበረሰብ ሰላሙን በንቃት በመጠበቅ ረገድ እያደረገ ያለው ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት አቶ አለማየሁ የልማት ስራዎች ያለምንም ስጋት እንዲከናወኑ ህዝቡ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *