በአካቢው የንጹህ መጠጥ ውሃ ማግኘት በመቻላቸው መደሰታቸውን ነዋሪዎች ገለጹ።

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ በቤንች ሸኮ ዞን በሸኮ ወረዳ የግዝ መሬት- ሺም የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክት ከዘላቂ የልማት ድርጅት ፕሮጀክት (SDG) በተገኘው 34 ነጥብ 7 ሚለየን ብር የበጀት ድጋፍ የተገነባው ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል ።

ያነጋገርናቸው የግዝ መሬትና ሺሚ ቀበሌ ነዋሪዎች በቀበሌው የንጹህ ውሃ ተመርቆ አገልግሎት ማግኘት በመቻላቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።

ከዚህ በፊት በቂ የሆነ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ባለመኖሩ ሲቸገሩ እንደቆዩ ያስታወሱት አስተያየት ሰጪዎቹ አሁን በቀበሌው ዘላቂና አስተማማኝ ንጹህ የመጠጥ ውሃ እየቀረበላቸው እንደሆነም ነው የገለጹት።

የተጠቃሚ ማህበረሰብ ክፍልና የቀበሌው ነዋሪዎች አቶ ሰይድ ይመር፣ ፍቃዱ ደበላና ወ/ሮ አስካለ አበበ በሰጡት አስተያየታቸው ይህ ተጀምሮ ተቋርጠው የቆየውን ግንባታ በጀት መድቦ በአጭር ጊዜ መጠናቀቁ የአዲሱ ክልል የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ የሰጠው ትኩረትና የለውጥ መንግስት ውጤት መሆኑን አንስተዋል ።

በመሆኑ ከዚህ በፊት በአካባቢው የነበረው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነት ችግር በዘላቂነት ከመፈታቱ ባሻገር ለረዥም ጊዜ ወረፋን በመጠበቅ የሚባክነውን ጊዜ ለተለያዩ ስራ እንዲውል በማትረፋቸው መደሰታቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ገልጸዋል ።

የክልሉ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ምክትል ኃላፊና የንጹህ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ዘርፍ ኃላፊ ኢንጂነር ፈልታሞ ዲብሎ ፕሮጀክቱ በነባሩ ክልል ተጀምሮ ለረዥም ጊዜ ተቋርጦ የቆየና በ2015 ዓ/ም እንደገና በጀት በመመደብ፣ ውል በመግባት በመልካሙ ግዛው የስራ ተቋራጭ ተገንብቶ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት መደረጉን ገልጸዋል ።

የውሃ ፕሮጀክቱ ከዚህ በፊት ሲነሳ የነበረውን የህብረተሰቡን የመልማትና የመሠረተ ልማት ጥያቄን ከመመለስም በላይ የተደራሽነትን ችግር መቅረፉን አንስተዋል ።

ግንባታው በአጭር ጊዜ መጠናቀቅ የክልሉ መንግስትና ቢሮው በሰጠው ትኩረት እውን መሆኑን አንስተዋል።

ፕሮጀክቱ 23 የውሃ ቦኖ፣ 200 ሜትር ክዩብ መያዝ የሚችል የውሀ ማጠራቀሚያ ጋንዳ፣ 2.2 ኪሎ ሜትር ከጥልቅ ውሃ ጉድጓድ እስከ ማጠራቀሚያው ዋና መስመር ዝርጋታ፣ 8.44 ኪ/ሜ የማሰራጫ መስመር፣ የጀኔረተር ቤት ግንባታ፣ ጀኔረተርና የፓንፕ ተከላ ስራን ያካተተ እና አጠቃላይ 34,762, 930.72 ብር በጀት መፍጀቱን ጨምረው አብራርተዋል ።

በመሆኑም የህብረተሰብ ተጠቃሚነትን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ህብረተሰቡ የውሃ አስተዳደር ስርዓትን በማጠናከር፣ በተመጣጣኝ ክፊያ ገቢን በማሰባሰብ ተቋሙን መንከባከብ እንደሚገባ በማሳሰብ የክልሉ ውሃ ተቋማት አሰተዳደር ዳይሬክቶረት ቀጣይነት ያለውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል ።

የሸኮ ወረዳ ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤተ ኃላፊ አቶ ዘማች ደመቀ ክልልሉ የግንባታ ወጪውን ሙሉ በሙሉ በመሸፈንና የቅርብ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቁ አመስግነዋል።

የተገባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋም የግዝ መሬትና ሺሚ ቀበሌ ውሃ ችግር ከመፍታትም በላይ የወረዳውን የውሃ ሽፋን እንደሚያሳግ ገልጸዋል ።

ፕሮጀክቱ 6337 የግዝ መሬት እና ሺሚ ቀበሌ የህብረተሰብ ክፍልን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

በጌታሁን ግርማ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *