






የካፈቾ ብሔር ቱባ ባህላዊና ታሪካዊ ዕሴት ያለውና እነዚህንም የማህበረሰቡ ተውፊቶች ጠብቆ ማቆየት የቻለ ማኅበረሰብ ነው።
ከእነዚህ የብሔሩ ባህላዊ ሀብቶችና ክዋኔዎች መካከል አንዱ ደግሞ ዛሬ በድምቀት እየተከበረ የሚገኘው የዘመን መለወጫ በዓል የኾነው (ማሽቃሮ) ነው፡፡
ማሽቃሮ በየዓመቱ መስከረም አጋማሽ የብሄረሰቡ ተወላጆች እና ወዳጆች ተስብስበው የነገስታት መናገሻ በኾነውና ከቦንጋ ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው “ቦንጌ ሻምበቶ” በጋራ የሚያከብሩት በዓል ነው።
የካፊቾ ብሔር ማሽቃሮ ከመድረሱ አስቀድሞ አዝመራን መሠረት ያደረገ የጊዜ ስሌት ወይም ቆጠራ የሚያደርግ ሲሆን የቀን ቆጠራውም ወርሃ ሐምሌ በገባ በአምስተኛው 77 ብሎ የሚጀምር ሲሆን ይኸም ለማሽቃሮ 77 ቀናት ቀሩት ተብሎ ይወሰዳል።
የአዝመራ ወቅትን መሠረት ያደረገው የቀን ስሌት 77 ቀናት ሲጠናቀቁ መስከረም 12 ወይም 13 ላይ የካፈቾ ብሄር የዘመን መለወጫ በዓል (ማሽቃሮ) ይሆናል ማለት ነው።
በዚህም መሠረት የዘንድሮ ማሽቃሮ በተለያዩ ባህላዊ ክንዋኔዎች ታጅበው የነገስታት መናገሻ “ቦንጌ ሻምበቶ” እየተከበረ ይገኛል።
በማሽቃሮ በየደረጃው ያሉ የባህላዊ ምክር ቤት (ምክረቾ) መሪዎች የስራ አፈጻጸማቸውን የሚያስገመግሙበት፣ የስልጣን ሹም ሽር የሚደረግበት እንዲሁም በአብዛኛው ከአስተዳደራዊ ስርዓት ጋር የሚገናኙ ተግባራት የሚፈጸምበት በዓልም ነው።
በዚህ በዓል ላይ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚሰቀል የወቅቱ የካፋ ባንዲራ ሌላኛው የበዓሉ ድምቀት ነው፡፡ ነጭ፣ ሰማያዊና ቀይ ህብረ-ቀለማት ያሉት ሰንደቅዓላማ በዓሉ በሚከበርበት ስፍራ በባህላዊ አስተዳደር (የምክረቾ) አባላት ይሰቀላል።
እያንዳንዱ ሰንደቅዓላማ ቀለም የሚያመለክተው እና የሚወክል ትርጉም እንዳለውም ነው የብሔረሰቡ የባህል አዋቂዎች የሚገልጹት።
የካፋ ህዝብ የራሱ የሆነ የንግሥና ስርዓት ያለው ሲሆን የንግሥናውን ስልጣን የሚሰጡትም ሰባቱ የባህላዊ ምክር ቤት (ምክረቾ) አባላት ናቸው፡፡
የዘንድሮው ማሽቃሮ በዓልም የባህላዊ ምክር ቤት (ምክረቾ) አባላት፣ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች፣ የብሔረሰቡ ተወላጆች እና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በዕድገቱ በዛብህ
