የወባ ስርጭትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የማህበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑ ተጠቆመ

Spread the love

በሸካ ዞን የማህበረሰብ አቀፍ የወባ መከላከል ስራዎች እና በወሳኝ የጤና ተግባራት ዙሪያ የባለድርሻ አካላት ንቅናቄ መድረክ በማሻ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።

የንቅናቄ መድረኩን በንግግር የከፈቱት የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ እንደገለጹት ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ጤናማና አምራች ትውልድ መፍጠር ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው ብለዋል።

ወባና ሌሎች በሽታዎችን ከመከላከል ጎን ለጎን ማከምና ማዳን ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከጤና ዘርፉ ይጠበቃል ሲሉም አንስተዋል።

የሸካ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ እምሩ ወዬሳ እንደገለጹት የወባ ስርጭትን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ውስጥ የማህበረሰቡ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።

የእናቶችና ህፃናትን ሞት በመቀነስ በአጠቃላይ አምራች ትውልድ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና ርብርቡ የማይተካ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል አቶ እምሩ።

አቶ እምሩ አክለውም ከጤና መረጃ አያያዝና ጥንቅር ጋር ተያይዞ የሚስተዋለውን ክፍተት ለማረም መድረኩ በእጅጉ ጠቃሚ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የእንኳን ደህና መጣችሁ ያስተላለፉት የማሻ ከተማ ከንቲባ አቶ ሠራዊት አየነው በወቅቱ እንደተናገሩት መሠል መድረኮች በከተማው መካሄዱ ለከተማው መነቃቃት ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልፀው የመድረኩ ተሳታፊዎች በከተማው የሚኖራቸው ቆይታ ያማረና የሠመረ እንዲሆን ተመኝተዋል።

ለንቅናቄ መድረክ የሚሆን የመወያያ ሠነድ የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ እምሩ ወዬሳ እያቀረቡ የሚገኙ ሲሆን ሰፊ ውይይትም ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በመድረኩ የሸካ ዞን፣ የ3ቱ ወረዳና 2ቱ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች፣ በየደረጃው የሚገኙ የጤና ተቋማትና ጽ/ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ ሲል የዞኑ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *