







የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የተፎካካሪ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትና በክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ትብብር የተዘጋጀ የባለድርሻ አካላት ስልጠናና የቀጣይ አቅጣጫ መድረክ በሚዛን እየተካሄደ ይገኛል።
የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅሬ አማን ሀገራችን በማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ በፖለቲካዊና በዲፕሎማሲያዊ መስክ በከፍተኛ ለውጥና ስኬት ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ከሀገራዊ ለውጡ በፊት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ከተሰው ስያሜ ጀምሮ ምህዳሩ በመፈራረጅ ፣ በመገፋፋት ፣ በጋራ ከመስራት ይልቅ በተናጥል መስራት ላይ የተመሰረተ እንደነበረ ጠቁመዋል ።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የፖለቲካ ስነ ምህዳሩን የማስፋት ፣ ሀገርን በጋራ የማጽናትና የመታደግ ፣ አብሮ የመስራትና መበልጽግን እውን ያደረገ አካታች የፖለቲካ ስርዓትን መዘርጋት ተችሏል ብለዋል።
መሪው ፓርቲ ብልጽግናም በሀገራችን የፖለቲካ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አካታች የፖለቲካ ስርዓትን እውን በማድረግ ከፌደራል ጀምሮ አስከ ወረዳ ድረስ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮችን በመሾም በጋራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከፌደራል ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትን በማቋቋም እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል። በዚህም በክልሉ 10 ሀገራዊና 3 ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው እንደሚሳተፉም ገልጸዋል።
ምርጫው ሰላማዊ ፣ ዲሞክራሲያዊ ፣ ፍትሀዊና አካታች እንዲሆን ገዥው ፓርቲ በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል ሲሉ ገልጸዋል። ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በተቋቋሙ የጋራ ምክር ቤቶች በንቃት የመሳተፍ ፣ የመወያየትና ችግሮችን እየፈቱ መሄድ ይገባል ብለዋል።
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ ፣ ፍትሀዊና አካታች በማድረግ ለአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌት የሚሆን ለማድረግ የሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አቶ ፍቅሬ አሳስበዋል ።
በመድረኩ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ካሳን ጨምሮ በሀገራዊ ምርጫው የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የተገኙ ሲሆን የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ምትኩ ታምሩ የመወያያ ሰነድ እያቀረቡ ይገኛሉ ሲል ቤንች ሸኮ ቴቪ ዘግቧል።
