ቲካሻ ቤንጊ አሰባሳቢ ፣ አንድነትን ፈጣሪና ባህልና ቋንቋን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማሸጋገር ድልድይ መሆኑን የብሔረሰቡ ተወላጆች ተናገሩ።

Spread the love

በዓሉ ሰላምን የማጽናት ፣ ልማትን የማረጋገጥና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክር በመሆኑ የቅድመ ዝግጅት ስራው በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አዘጋጅ ኮሚቴው ገልጿል።

የሸኮ ብሔር የአዲስ ዘመን ብስራትና የምስጋና በዓል የሆነው ቲካሻ ቤንጊ ለዘመናት ተቋርጦ ከቆየበት ባለፉት 2 አመታት የብሔረሰቡ ተወላጆችና እንግዶች በተገኙበት በሸኮ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

የብሔሩ ተወላጆች ከሆኑት ውስጥ አቶ አዲሱ በዲ ፣ ኤፌሶን ሱብሳ ፣ ገሰን መርጋና መላኩ ፊጣ እንደተናገሩት ቲካሻ ቤንጊ ሰላም ፣ አንድነትና አብሮነት በስፋት የሚንጸባረቅበት የአዲስ አመት ብስራትና የምስጋና በዓል ነው ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት አመታት ለዘመናት ተቋርጦ ከነበረበት በአዲስ መልክ መከበር መጀመሩ በብሔሩ ተወላጆች ዘንድ ከፍተኛ መነቃቃትና ወጣቱ ትውልድ ወደ ባህሉ፣ ቋንቋውና እሴቶቹ እንዲመለስ አስችሏል ብለዋል።

ቲካሻ ቤንጊ በተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው ይኖሩ የነበሩ የብሔረሰቡ ተወላጆች ወደ አንድ ማዕከል እንዲሰባሰቡና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር ማስቻሉንም ገልጸዋል።

የቲካሻ ቤንጊ በዓል አከባበር አብይ ኮሚቴ ጸሐፊ አቶ አዲሱ ዱዳብ በበኩላቸው ቲካሻ ቤንጊ የሸኮ ብሔር የአዲስ ዘመን ብስራትና የምስጋና በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉ ከክረምቱ ጎርፍ ፣ ጭጋግና መብረቅ ፈጣሪ ጠብቆ ለበጋው ወቅትና ምርት በመድረሳቸው የሚቀርብ ምስጋናና የምርት ቅምሻ በዓልም ነው ብለዋል።

በቲካሻ ቤንጊ የተጣሉ የሚታረቁበት ፣ ያመረቱ ሌሎች ምርት በማካፈል በጋራ የሚቀምሱበት የሰላም ፣ የፍቅር ፣ የአንድነትና የአብሮነት በዓል በመሆኑ ለብሔሩ ተወላጆች ትልቅ ትርጉም ያለው ነው ብለዋል።

በዓሉን ለ3ኛ ዙር በድምቀት ለማክበር አዘጋጅ ኮሚቴው ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን አቶ አዲሱ ጠቅሰው በዓሉ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የብሔሩ ተወላጆች እና ባላባቶች በተገኙበት በድምቀት ይከበራል ማለታቸዉን የቤንች ሸኮ ቴቪ ዘገባ ያመለክታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *