







የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ (ዶ/ር) በካፋ ዞን የቢጣ ዳካ መንገድ፣ የሜኒ ወንዝ ድልድይ እንዲሁም የቢጣ ገነት ከተማ የንጹህ መጠጥ ዉሃ ፕሮጀክቶችን መርቀው ከፍተዋል።
በምረቃው ሥነ ሥርዓት ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) የለውጡ መንግሥትና ፓርቲዉ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ አከባቢዎችን በልማት ተጠቃሚ ለማድረግ ሕብረተሰቡን በማስተባበር ፈጠራና ፍጥነት በታከለበት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለዚህም በካፋ ዞን ቢጣ ወረዳ ተገንብተው የተመረቁ የቢጣ ዳካ መንገድ፣ ድልድይ እና የቢጣ ገነት ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም የንግድ፣ ጤና፣ የትምህርት እና ሌሎች የማህበራዊ አገልግሎቶች ተደራሽነት እንዲጨምር አጋዥ ነው ብለዋል።
በቀጣይ መብራትና የኔትወርክ አገልግሎት ጨምሮ ሌሎች የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በቁርጠኝነት ይሰራልም ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
ቢጣ ወረዳ ግብርና ምርቶች በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች መካከል ተጠቃሺ እንደሆነ የገለፁት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸዉ ናቸው።
የመንገዱ ግንባታ የእርሻ ምርትን ወደ ገበያ ለማቅረብ ዕድል እንደሚፈጥር የጠቀሱት አቶ ማስረሻ ማህበረሰቡ ዕድሉን በመጠቀም ምርቶች ካለፉት ጊዜያት በተሻለ ወደ ገበያ ማቅረብና ተጠቃሚነታቸውን ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጂዮ ሳፒ በክልሉ የመንገድና የድልድይ ልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ ከመንግስት በጀት በተጨማሪ ማኅበረሰቡን በማሳተፍ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
አቶ ፋጂዮ ሳፒ ጨምረውም የተመረቁ የቢጣ ደካ መንገድና የሜኒ ወንዝ ድልድይ ፕሮጀክቶች ለረጅም ጊዜያት አገልግሎት እንዲሰጡ ህብረተሰብ እንዲንከባከብና እንዲጠብቅ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዞኑ የሕብረተሰቡ የልማት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየተሰሩ ያሉ ተግባራት በቀጣይነት ተጠናክሮ ይቀጥላሉ ሲሉ የካፋ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ደመላሽ ንጉሴ ተናግረዋል።
የቢጣ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ ዳግማዊ ማሞ በበኩላቸው የተመረቁ የልማት ፕሮጀክቶች የዘመናት የህዝቡ የልማት ጥያቄዎችን በተጨባጭ የመለሱ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በፍቅር ከበደ
