




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የደን፤ አካባቢ ጥበቃና አየር ንብረት ለውጥ ቢሮ FOLUR ፕሮጀክት ከክልሉ ቡና ሻይና ቅመማ፤ ቅመም ባለስልጣን ጋር በመተባበር የቡና ምርታማነት ለማሻሻል ያለመ የምክክር መድረክ በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የክልሉ ደን፣ አከባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አስራት ገብረማሪያም (ዶ/ር) ክልሉ እምቅ በተፈጥሮ ሀብቶች የሚታወቅ በሀገር ደረጃ ግንባር ቀደም የሆነ አከባቢ እንደሆነ ገልጸዋል።
በክልሉ ካሉ በርካታ የተፈጥሮ ጸጋዎች መካከል አንዱ የሆነው ቡና ለኢኮኖሚ ምንጭ፣ ለማህበረሰቡ ኑሮ መሻሻልና ለውጪ ምንዛሬ ግኝት አስተዋጽኦዉ የጎላ ነው።
በክልሉ በዘመናዊ መንገድ የቡና ምርታማነት በማሳደግ የማኅበረሰቡን ኑሮ ለመቀየር እና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራም ኢንጂነር አስራት ገብረማርያም (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በክልላችን በርካታ መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት ድርጅቶች እንዳሉትም ያነሱት ዶክተር አስራት ከእነዚህም ውስጥ folur ፕሮጀክት አንዱ እንደሆነም አንስተዋል።
FOLUR ፕሮጀክት በክልላችን በሁለት ዞኖች ማለትም በካፋና በቤንች ሸኮ ዞኖች በስድስት ወረዳዎች በመንቀሳቀስ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግቧል ነው ያሉት።
በክልሉ በFOLUR ፕሮጀክት የተጀመረውን ውጤታማ ሥራዎችን ለማስፋፋትና የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እንደሚሰራ ነው ኢንጂነር አስራት ገብረማሪያም (ዶ/ር) የገለጹት።
የክልሉ ቡና፣ ሻይና ቅመማቅመም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት መኩሪያ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የአከባቢ ፖቴንሽያል መሠረት በማድረግ ቡናን በብዛት በጥራት ለማምረት እንደሀገር የተለያዩ ኢንሼቲቭ ተቀርጸዉ ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል።
በክልል በአራቱም የአመራረት ዘዴዎች 597 ሺህ ሄ/ር በላይ የቡና ሽፋን ያለ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አስራት የቡና ምርታማነት ክልሉ ካለው አቅም አንፃር አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
በ2013 የምርት ዘመን ከ77 ሺህ ሄ/ር በላይ የቡና ማሳ ምርታማነት በተለያዩ ምክንያቶች መቀነሱን የተለየ ሲሆን ባለፉት አራት ዓመታት በተከናወነ የቡና ምርታማነት ፓኬጅ ማዘመን ስራ 14 ሺህ ሄ/ር የሚጠጋ የቡና ማሳ ማደስ መቻሉን ተናግረዋል።
በቀጣይ በሚከናወኑ የቡና ምርታማነት ማሳደግ ስራዎች የቡና ማሳ እድሳትና ሌሎች የቡና ጥራት ማሻሻያ ስራዎች የሚከናወኑ መሆናቸውን አቶ አስራት ገልጸዋል።
