የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ-ግብር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በተግባር እያገዘ ይገኛል

Spread the love

የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ-ግብር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት በተግባር እያገዘ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) አነሳሽነት ተግባራዊ የተደረገው የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ-ግብር በዓለም አቀፍ ደረጃ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ለሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቷል፡፡

መርኃ-ግብሩ የአሁኑን ትውልድ ተጠቃሚነት ያረጋገጠ እንዲሁም ለመጪው ትውልድ ተስፋን የሰጠ ሲሆን በስራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አኳያ ሚናውን እየተወጣ ይገኛል፡፡

በዚህም ኢትዮጵያ በብራዚል ቤለም በተካሄደው የዓለም የአየር ንብረት(COP-30) ጉባኤ ላይ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት(COP-32) ጉባኤን እንድታስተናግድ መመረጧ ይታወቃል።

በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብት ልማትና አጠቃቀም መሪ ስራ አስፈጻሚ እና በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የብሄራዊ ቴክኒክ ኮሚቴ ጸሃፊ ፋኑሴ መኮንን፤ የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ-ግብር ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እያደረገች ላለችው ጥረት ተግባራዊ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡

ባለፉት ሰባት ዓመታት ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞች የተተከሉ ሲሆን አርባ በመቶ የሚሆኑት ሀገር በቀል ሲሆኑ ቀሪው የተለያየ ዝርያ ያላቸው መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡

አረንጓዴ ዐሻራ የአፈር መሸርሸርን በመቀነስና ለምነትን በመጨመር የግብርና ምርታማነት እንዲሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል።

የከርሰ ምድር የውሃ አቅምን በማሳደግ የመስኖ እርሻዎች እንዲስፋፉም የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት ለምግብነት አገልግሎት የሚውሉ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ጨምሮ ሌሎች ችግኞች በስፋት መተከላቸውን ጠቁመው፤ እነዚህም ለቤተሰብ የገቢ ምንጭና ለሥርዓተ ምግብ መሻሻል ድርሻቸው ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ-ግብር የተተከሉ ችግኞች ደን በመሆን ለማር ምርት ምቹ ሁኔታ በመፍጠር የንብ አናቢዎችን ተጠቃሚነት እያሳደጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡

በበርካታ ዘርፎች ሰፊ የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር በተለይም የወጣቶችንና የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃ-ግብር ለድርቅ ተጋላጭ የሆኑና የተራቆቱ አካባቢዎች ወደ ምርታማነት እንዲለወጡ በማድረግ ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ የራሱን አስተዋጾኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስታውቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *