የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መተግበር ሥራዎችን በቅንጅት ለማከናወን አስችሏል – የፍትህ ሚኒስቴር

Spread the love

የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ፍኖተ ካርታ በፌደራል ደረጃ መተግበር ከጀመረ ወዲህ በሀገር ደረጃ የወንጀል፣ የፍትሀ ብሔር እና የአስተዳደር ፍትህ ሥራዎችን በቅንጅት ለማከናወን መቻሉን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የአማራ ክልል የዳኝነትና የፍትህ አካላት የትብብር ጥምረት መድረክ በሦስተኛ ቀን ውሎው የፌዴራል ፍትህ ተቋማት የለውጥ ሥራዎች ተሞክሮና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አተገባበር ላይ መክሯል።

በሚኒስቴሩ የተቋም ግንባታና ሪፎርም ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ አቶ አማኑኤል ታደሰ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፣ የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ፍኖተ ካርታ ካለፈው ዓመት ጀምሮ በፌዴራል ደረጃ እየተተገበረ ይገኛል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በፍትህ ዘርፍ ቀደም ሲል ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን ለማስተካከልና የህብረተሰቡን አመኔታ ለማሳደግ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ከተሰሩ ስራዎች መካከል የፌዴራል ፍርድ ቤቶች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች፣ የማረሚያ ቤቶች እና ሌሎች የህግ ማሻሻያ አዋጆች ፀድቀው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቅስዋል።

ይህም በወንጀል፣ በፍትሃ ብሔር እና በወንጀል አስተዳደር ላይ ይታዩ የነበሩ የህግ ክፍተቶች ህጋዊ ማዕቀፍ እንዲኖራቸው አስችሏል ነው ያሉት።

እንደአማካሪው ገለጻ በተለይ የፍትህ ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራን ተከትሎ በፍትህ ዘርፉ የሚገኙ ተዋንያን ሥራዎችን በጋራ ከመስራትና ከመገምገም ባለፈ ክፍተቶችን ለይተው ማረማቸው ለውጦች እንዲመዘገቡ አድርጓል።

ይህም ከወንጀል፣ ከፍትሃ ብሔር እና የአስተዳደር ፍትህ መረጃን ከማጠናከር፣ ክስ ከመመስረት፣ ከማስቀጣት እስከ ማረም ድረስ ይታዩ የነበሩ ችግሮች እንዲቃለሉ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ የፍትህ ተቋማት የሚሰጧቸውን አገልግሎቶች ዲጂታላይዝ በማድረግ የተገልጋዩን ህብረተሰብ አመኔታ ለማሳደግ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙም አቶ አማኑኤል አመልክተዋል።

በፌደራል ደረጃ በ2012 ዓ.ም ወጥቶ እየተተገበረ ያለው የአስተዳደር ፍትህ አዋጅን ሁሉም ክልሎች በራሳቸው አጽድቀው በመተግበር የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።

የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ በበኩላቸው፣ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተሰሩ ሥራዎች ታራሚዎች ሰብዓዊ መብቶቻቸው ተከብሮ ታርመውና ታንፀው ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

ይህም ከለውጡ በፊት የነበረ የከፋ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዲቀንስ ከማድረጉም በላይ ታራሚዎች ያለምንም ችግር ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ ለማድረግ ማስቻሉን ገልጸዋል።

ታራሚዎች በፍርድ ቆይታቸው የተለያየ ሙያ ባለቤት እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ ታርመው ሲወጡ የራሳቸውን ሥራ እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም ነው ያመለከቱት።

እንዲሁም ለታራሚዎች ሞቹ ያልሆኑና ያረጁ ቤቶች በአዲስ ተገንብተው ጤንነታቸው እንዲጠበቁ የማድረግ ሥራ መከናወኑንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ተልዕኳቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አመራሮችን በአዲስ የመተካት ሥራ መሠራቱን ጠቁመው፤ በትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ መሰረት የመጡ ለውጦችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል።

ከዚህ ጎን ለጎን ማረሚያ ቤቶች በቴክኖሎጂ ታግዘው የጥበቃ፣ የማረምና የማነጽ ሥራቸውን በአግባቡ እንዲያከናውኑ አቅጣጫ ተወስዶ እየተሰራ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *