
አባትም ልጅም የአንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች ናቸው።
ፕሮፌሰር ባዬ ይማም (አባት) እና ፕሮፌሰር ቃለአብ ባዬ ይማም (ልጅ) ዩኒቨርሲቲው ያፈራቸው ምሁራን።
ሁለቱም የከፍተኛ ትምህርት ህይወታቸውን በዚሁ አንጋፋው ዩኒቨርሲቲያችን ጀምረው በሞያቸው ዩኒቨርሲቲያችንን እያገለገሉና ተተኪ ምሁራንን እያፈሩ የሚገኙ ፕሮፌሰሮች ናቸው ሲል ይገልጻቸዋል ዩኒቨርሲቲው በማህበራዊ ትስስር ገጹ።
ፕሮፌሰር ባዬ ይማም 44 ዓመታትን እንዲሁም ፕሮፌሰር ቃለዓብ ባዬ ደግሞ 15 ዓመታትን በመምህርነት፣ በተመራማሪነት፣ እንዲሁም በተለያዩ የስራ ሀላፊነቶች ያገለገሉ እና እያገለገሉ የሚገኙ ምሁራን ናቸው።
የሁለቱም ተመሳሳይ ገጠመኝ ደግሞ የፒኤችዲ ዲግሪያቸውን በሰሩ ልክ በ10ኛው አመት የሙሉ የፕሮፌሰርነት ማዕረግን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ መሆናቸው ነው።
ፕሮፌሰር ቃለዓብ ባዬ በዘንድሮው ዓመት ዩኒቨርሲቲው የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ከሰጣቸው ምሁራን መካከል ናቸው።
ማዕረጉ የተሰጣቸው በማስተማር ውጤታማነት፤ ባሳተሟቸው 13 ጥናታዊ ጹሁፎች፤ ለማህበረሰብ ላበረከቱት አካዳሚያዊ አገልግሎትና በዩኒቨርሲቲው በነበራቸው የተቋም አስተዳደር ድምር ውጤት መሆኑንም ዩኒቨርሲቲው ገልጿል ያለው ኢዜአ ነው።
