በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃት ለመከላከል የባለድርሻ አካላት ድጋፍ መጠናከር እንዳለበት ተጠየቀ

Spread the love

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በሴቶች ላይ በሚደርሰው ጾታዊ ጥቃት የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የሚረዳ ስልጠና ለባለድርሻ አካላት በቦንጋ ከተማ እየሰጠ ይገኛል።

ስልጠናው በሴት ልጅ ግርዛትና የልጅነት ጋብቻ ላይ የማህበረሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ የስነ-ልቦናና ማህበራዊ እንዲሁም የህግ አገልግሎቶች አቅርቦትና ጥራት ማሻሻልና መደገፍን አላማ አድርጎ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።

በስልጠናው ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፌ-ጉባኤ ወ/ሮ ፀሀይ ደርጫ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሰውን ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ቀውስ ለመከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ወ/ሮ ፀሀይ አክለው የወንጀል ድርጊቱ ተፈጽሞ ስገኝ የህግ ተጠያቂነት ከማስፈን በተጓዳኝ ለጎጂዎችን የስነ-ልቦና ድጋፍ እንዲሁም የህግ ጉዳይ ማማከር ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ ቢሮው ከረጂ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት በዚህ ዘርፍ እየሰራ ያለው ተግባር አበረታች በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የችግሩ ስፋት አሳሳቢ በሆነባቸው ሁለት የክልሉ ዞኖች በሚገኙ 4 ወረዳዎች በአጠቃላይ 1መቶ 29 ቀበሌዎች በዩኒሴፍ ድጋፍ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃት ለመከላከል የተጀመረው ተግባር ተጨባጭ ውጤት እያመጣ መሆኑን ነው የክልሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትልና የሴቶች ሕጻናት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሪት ለምለም አምሳል የጠቆሙት።

የመጣው ውጤት የተገኘው በተከታታይ ስልጠናና ድጋፍ መሆኑን የገለጹት ኃላፊዋ በቀበሌ ደረጃ የተቋቋመው ግብረሀይል የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎችን ግንዛቤ በማሳደግ ለውጡ እንደሚመጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በዚህም ግርዛት በወልድ ጊዜ የሚስተዋለውን ውስብስብ የጤና ችግር በመረዳት የመተው ዝንባሌ እንዲሁም ያለዕድሜ ጋብቻ የሚስተካከለውን ዘርፈ ብዙ ችግር በመረዳት የማስቀረት ባህል በማህበረሰቡ ውስጥ እያደገ መምጣቱን ኃላፊዋ አስረድተዋል።

የባለድርሻ አካላት ችግሩ እንዳይከሰት የማህበረሰቡን ግንዛቤ ከማሳደግ ጎን ለጎን ጾታን መሠረት ያደረገ ጥቃት ተፈጽሞ ስገኝ ለችግሩ ሰለባዋች የተቀናጀ የስነ-ልቦናና ማህበራዊ (pyscho-social support) ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው ያስገነዘቡት ወ/ሪት ለምለም ስልጠናው የባለድርሻ አካላት ሚናቸውን በመለየት ለቀጣይ ተግባር ራሳቸውን የሚያዘጋጁበት መሆኑን ገልጸዋል።

በስነ-ልቦናና ማህበራዊ ድጋፍ አሰጣጥ ዙሪያ በቢሮው ከፍተኛ ባለሙያ የስልጠና ስነድ እየቀረበ የሚገኝ ሲሆን በመድረኩ የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴዎች እና ሌሎች የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

በፍቅር ከበደ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *