በሀገር አቀፍ ደረጃ በተከናወኑ የኮሪደር ልማት ስራዎች ከ300 በላይ ፕሮጀክቶች ተጠናቀዋል – የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር

Spread the love

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ60 በላይ ከተሞች ላይ እየተከናወነ ባለው የኮሪደር ልማት ከ300 በላይ ፕሮጀክቶች በመጀመሪያው ዙር መጠናቀቃቸውን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከተሞች ተመራጭ የቱሪዝምና የኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዲሆኑ ታቅዶ እየተተገበረ የሚገኝ የልማት ፕሮግራም ነው፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወነውን የኮሪደር ልማት ስራዎች አስመልክቶ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ሔለን ደበበ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በሰጡት ማብራሪያ መንግስት ከተሞችን ለዜጎች ኑሮ ምቹና ተስማሚ ከማድረግ ባለፈ ለኢንቨስትመንት መዳረሻ እንዲሆኑ በልዩ ትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዚህም ከተሞች ያሏቸውን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሃብቶች በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እንዲያውሉ የሚያስችሉ የልማት ስራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

ከተሞች በፕላን የተመራ አሰራርን እንዲከተሉ ለማስቻል የከተሞች የመሬት አጠቃቀም ፕላን ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የከተማ መሬት አጠቃቀም ፕላን 30 በመቶ ለመንገድ፣ 30 በመቶ ለአረንጓዴ ልማት እንዲሁም 40 በመቶ ለግንባታ እንዲውል ተደርጎ መዘጋጀቱን ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጂ በርካታ ከተሞች አወቃቀርና አመሰራረታቸው በፕላን የተደገፈ ባለመሆኑ የመሬት አጠቃቀም ውስንነት እንዲፈጠር አድርጓል ነው ያሉት።

በዚህም በቂ መሰረተ ልማትን ያላሟሉና ከደረጃ በታች የሆኑ በርካታ ከተሞች መፈጠራቸውን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት በከተማ ፕላንና በመሬት አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ ውስንነቶችን ለመሙላት በእጅጉ እያገዘ ስለመሆኑም ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውቀዋል።

የከተሞች ልማት መሰረታዊ ለውጥ እንዲያመጡ በማድረግ በኩል የኮሪደር ልማቱ ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል ነው ያሉት።

እንዲሁም አረንጓዴ ስፍራዎችን ለማስጠበቅ፣ ያለአግባብ ታጥረው የቆዩ መሬቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ አስቻይ ሁኔታን መፍጠሩን ተናግረዋል።

በመሆኑም የዜጎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር ዘመናዊና ተወዳዳሪ ከተሞችን ለመገንባት የኮሪደር ልማቱ ትልቅ መነቃቃት መፍጠሩን ጠቅሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የኮሪደር ልማት ስራዎች በሁሉም ክልሎች ባሉ 60 ከተሞች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

ከእነዚሀ ውስጥ ከ30 በላይ ከተሞች የመጀመሪያውን ዙር አጠናቀው ወደ ሁለተኛው ዙር መሸጋገራቸውን ገልጸው፤ ለስኬታማነቱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም ከ300 በላይ ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው አገልግሎት መጀመራቸውን ጠቁመው፤ የፕሮጀክቱ አካል የሆኑና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ግንባታዎች መካተታቸውን ገልጸዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *