




በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ “ትውልድ በመምህር ይቀረጻል ፤ ሀገር በትምህርት ይበለጽጋል” በሚል መሪ ቃል የመምህራን ውይይት እየተካሄደ ነው።
የመድረኩን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲው ተጠባባቂ ፕረዝደንት ዶክተር ደገላ ኤርገኖ ፤ የዚህ ሀገር-አቀፍ መድረክ ዓላማ የመምህራንን ሀሳብ ለማድመጥና እርስ-በእርስ ለመወያየት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ የምትፈጋቸውን በሳልና በማመዛዘን የፈለቁ የምሁራን ሀሳቦችን ለማስተናገድ ታስቦ እንደሆነም አብራርተዋል።
መንግስት ለሚሰራቸው ስራዎች ግብዓት የሚሆኑ ሀሳቦችን ከምሁራን ለማግኘትና ተግባራዊ ለማድረግ በሀገር-አቀፍ ደረጃ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ውይይት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው መምህርነት የሙያ ፍቅርን መሠረት በማድረግ ለሀገር ጠቃሚ ዜጎችን የሚያፈሩበት የተከበረ ሙያ ነው ብለዋል።
አቶ ማስረሻ ፤ ሀገራዊ ለውጡ አሁን የደረሰበትን ደረጃና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በሚመለከት ባቀረቡት የመወያያ ሰነድ አሰባሳቢ ትርክትን ለመፍጠርና ህብረ-ብሔራዊነትን ለማፅናት የመምህራን አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
የትምህርት ዘርፍ ሙያዊ ነፃነቱ ተጠብቆ እንዲቀጥልና ሀገርን መምራት የሚችሉ ምሁራንን ለማፍራት እንዲቻል በመንግስት ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን ነው የተናገሩት።
በትምሀርት ዘርፍ ከተከናወኑ የለውጥ ስራዎች መካከል ሙያዊ ነፃነትን ለማስከበር፣ የፈተና አሰጣጥንና አጠቃላይ የትምህርት ስርዓቱን ለማሻሻል መሰራቱን ጠቅሰዋል።
በዚህም የትምህርት ጥራትን በማረጋገጥ ተጨባጭ ለውጥ መታየት ጀምሯል ነው ያሉት።
የተወዘፉ ከባባድ የትምህርት ዘርፍ ችግሮችን በመለየት ባለፉት ሰባት ዓመታት ለውጥ መታየቱን ገልፀዋል።
በችግሮች ላይ የማስተካከያ ርምጃ በመውሰድና ለቀጣይ ስራዎችም የሚጠቅሙ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በመድረኩ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታዎችን እና የቀጣይ ስራ አቅጣጫዎችን የሚመለከት ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል።
በመድረኩ የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕረዝደንቶችና የስራ ኃላፊዎች፣ መምህራን እንዲሁም ሌሎችም ተሳትፈዋል ሲል ቦንጋ ኤፍኤም 97.4 ዘግቧል።
