








በኮንታ ዞን ኮይሻ ወረዳ በመገንባት ላይ ያለው የጽልቢ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክት ግንባታ ፊዚካል ስራው 90 ከመቶ ደርሷል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መስኖ ተቋማት ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ በክልሉ ያሉ አርሶአደሮችን በግብርና ልማት ስራዎች ምርታማ ለማድረግ የአነስተኛ መስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ እየሰራ ነው ።
በክልሉ በዘላቂ ልማት ግቦች በጀት ድጋፍ እየተገነቡ ከሚገኙ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክቶችመካከል የጽልቢ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው ።
ዝናብ አጠር በሆኑ አካባቢዎች እየተገነቡ ከሚገኙት መካከል አንዱ የሆነው የጽልቢ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክት በኮይሻ ወረዳ በ35 ሚሊዮን ብር እየተገነባ እንደሚገኝ በኤጀንሲው የመስኖ ተቋማት መሀንዲስ ኢንጂነር ቻላቸው ሸንቁጤ ናግረዋል ።
የጽልቢ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ ከ100 በላይ ሄክታር መሬት እንደሚያለማም ኢንጂነር ቻላቸው አስረድተዋል።
የመስኖ ግንባታው ውል ከተገባለት ጊዜ ባሉት 300 ቀናት ለማጠናቀቅ ቢጀመርም በአንዳንድ መሠረታዊ ተግዳሮቶች ስራው ሊጠናቀቅ እንዳልተቻለ አብራርተዋል ።
አሁን ላይ በግንባታው ላይ የዲዛይን ማሻሻያ በማድረግና በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ በሙሉ አቅሙ ጥቅም ላይ እንዲውል የክልሉ መስኖ ተቋማት ልማት አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ እንደሚገኝ ተ
ኢንጂነር ቻላቸው ተናግረዋል ።
በገዛኸኝ ዋጄቦ ህንጻና ውሃ ስራዎች ተቋራጭ እየተገነባ ያለው ይኸው የጽልቢ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክት ለ150 ዜጌች ጊዜያዊ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን በፕሮጀክቱ ዋና ስራአስኪያጅ ቃኘው አማረ ተናግረዋል ።
የጽልቢ አነስተኛ መስኖ ፕሮጀክት ለአካባቢው አገልግሎት በከፊል እየሰጠ እንደሚገኝና በቀሪ ጊዜያት ቀሪዎቹን ስራዎች ለማጠናቀቅ ትኩረት በመስጠት እየሰሩ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
ፕሮጀክቱ 139 ሜትር የሚረዝም ተንጠልጣይ ዋና ቦይ እየተገነባ እንደሚገኝም ስራአስኪያጅ ቃኘው አማረ ተናግረዋል ።
የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወጣቶች መካከል አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት ፕሮጀክቱ በአካባቢው መገንባቱ ለበርካታ ወጣቶች የኢኮኖሚ ችግሮቻቸውን መፍታት እንደቻለ ተናግረዋል ።
በታጠቅ አበበ
