የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን መከበር ለባህል፣ ለቋንቋ፣ ለዲሞክራሲና ለሀገራዊ አንድነት መገንባት ፋይዳው የላቀ መሆኑን የበዓሉ ተሳታፊዎች ተናገሩ

Spread the love

19ኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ቀን ክልላዊ ማጠቃለያ መድረክ በተለያዩ ሁነቶች በቴፒ ከተማ ተከብሯል።

በበዓሉ ላይ ከክልሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉ ሲሆን የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ቀን መከበሩ ለባህል፣ ለቋንቋ፣ ለዲሞክራሲና ለሀገራዊ አንድነት መገንባት ፋይዳው የላቀ መሆኑን ተናግረዋል ።

የበዓሉ መከበር አንድነትን የምናጠናክርበትና ብዝሃነት የሚረጋገጥበት ነው ሲሉም አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል ።

በብዝሃነት ውስጥ አንድነትን ለማምጣት በመደማመጥና በመከባበር ህገ መንግስታዊ ስርዓቱን ማክበር ከሁሉም ዜጋ የሚጠበቅ ኃላፊነት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።

የብሔሮች ብሔረሰቦች ህዝቦች ቀን በዓል መነሻው ህገመንግስት ነው ያሉት አስተያየት ሰጪዎቹ የዲሞክራሲ ስርዓት እውን እንዲሆን የህግ የበላይነት ሊከበር ይገባል ሲሉም ተናግረዋል ።

በ19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦች ህዝቦች ቀን በዓል ላይ በቀረበው የውይይት መነሻ ጽሑፍ ከተሳታፊዎች አስተያየቶች ተሰጥተዋል።

በዚህም ህብረብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር የህግ የበላይነትን ማክበርና ብዝሃነትን አጠናክረን ማስቀጠል ይጠበቅብናል ሲሉም ተናግረዋል ።

ክልላዊ የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲጎለብትና የህግ የበላይነት እንዲከበር በተቋማት ግንባታ ላይ መስራት ትኩረት የሚሰጠው ተግባር መሆኑን የገለጹት የክልሉ ምክርቤት ምክትል አፈጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ጸሐይ ደርጫ ናቸው ።

ምክትል አፈጉባኤዋ የበዓሉ መከበር ለሀገራዊ መግባባት እና ህብረብሔራዊ አንድነት መጠናከር ላይ ያሉብንን ስብራቶች የምናጠናክርበት እንደሆነም ተናግረዋል ።

የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ የተከበሩ አቶ መቱ አኩ በክልሉ ለ3ኛ ጊዜ እንደ ሀገር ለ19ኛ ጊዜ የሚከበረው ይኸው በዓል ፌዴራሊዝም ስርዓት እና ህገመንግስታዊ ስርዓቱ እንዲዳብር መሠረት የሚጥል ነው ብለዋል።

በዚህም ትውልዱን የሚያንጹ ስራዎችን መስራት ከሁሉም አካላት የሚጠበቅ ተግባር መሆኑን አቶ መቱ አኩ አመላክተዋል ።

በሀገርም ሆነ በክልሉ የህግ የበላይነት እንዲከበር መንግስት እየሰራ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ መቱ አኩ ይኸው የበለጠ እንዲጠናከር የሐይማኖት አባቶች ፣የሀገር ሽማግሌዎች ፣የመንግስት አካላትና የጸጥታ አካላት በትብብርና በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባቸው አሳስበዋል ።

በ19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦች ህዝቦች በዓል ቀን ክልሉን ወክለው 196 ልዑካን በአርባምንጭ ከተማ እንደሚሳተፉም አቶ መቱ ገልጸዋል።

19ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦች ህዝቦች በዓል ቀን ክልላዊ ማጠቃለያ በተለያዩ ሁነቶች የተከበረ ሲሆን የፌደራሊዝምና ህገ_ መንግስታዊ ስርዓቱን የተከተለ የጥያቄና መልስ ውድድር በማድረግ ለአሸናፊዎች የዕውቅናና ሽልማት ስነስርዓት በማከናወን ተጠናቅቋል ።

በታጠቅ አበበ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *