




የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ባከናወናቸው የተቀናጁ የልማት ስራዎች፣ 15,206 የሚሆኑ የገጠር ልማታዊ ሴፍትኔት ተረጂዎችን ማላቀቅ መቻሉ ተገልጿል።
የክልሉ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽኑ ኮሚሽነር ለማ መሠለ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ 23,669 የሴፍትኔት ተረጂዎች ውስጥ ፣ በተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት 15,206 የሚሆኑ ዜጎችን በማስመረቅ ከተረጂነት እንዲላቀቁ የተደረገ ሲሆን ቀሪዎችን በቀጣይ ወራት ለማስመረቅ የተቀናጀ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።
ቀልጣፋና ውጤታማ የአደጋ ምላሽ፤ ዝግጅትና የተቀናጀ ምላሽ ከመስጠት አንጻር ለቋሚና ጊዜያዊ ቀጥታ ተጠቃሚዎች ወቅታዊ ክፊያ ማስተላለፍ መቻሉንም አክለዋል።
የፋይናንስ ድጋፍ፡ በልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም ለ3,258 ቋሚና ጊዜያዊ ቀጥታ ተጠቃሚዎች እንዲሁም ለ20,411 የማህበረሰብ ስራ ተሳታፊዎች በድምሩ ከ 71 ሚሊዮን ብር በላይ ክፍያ 100% መፈጸሙ ተገልጿል።
የቁጠባ ባህልን መቀየርና ተጨማሪ ገቢ ማገኛ መንገዶችን ከማስፋት አንጻር ለ780 የቤተሰብ ኃላፊዎች የማይመለስ ገንዘብ ድጋፍ(Grant) ብር 25,974,400 በማቅረብ በተመረጡ የስራ አማራጮች ተሰማርተው ስር ከሰደደ ደህነት እንዲላቀቁ ድጋፍ ማድረግ መቻሉንም ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።
የቁጠባ ባህል ከጊዜ ወደ ጊዜ እንዲጨምር ለማድረግ ብር 2,217,600 ለማስቆጠብ ዕቅድ ተይዞ 100% መከናወኑን ጨምረው አንስተዋል።
ሰብአዊ ድጋፍን በራስ አቅም ምላሽ ለመስጠት 6684 ኩንታል እህል እና 2120 ሊትር ዘይት በመጠባበቂያ ክምችት መያዝ መቻሉንም ተናግረዋል።
በተለያዩ አደጋ ክስተት ጉዳት ለደረሰባቸው 1457 የህብረተሰብ ክፍሎች 448 ኩንታል የምግብ እህልና 280 ሊትር ዘይት ማቅረብ መቻሉንም አክለዋል።
በመኸር እርሻ ብቻ 546 ሄክታር ማሳ ለመጠባበቂያ ክምችት በዘር እንዲሸፈን ማድረግ የተቻለ ሲሆን ከዚህም 6320 ኩንታል ምርት መሰብሰብ መቻሉን ጨምረው አንስተዋል።
ለአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ፌንድ ስርዓት በመዘርጋት ሀብትን የማሰባሰብ ስራ እየተሰራ ያለ ሲሆን ከተለያዩ ምንጭ፤ ከህዝብ፣ ከመንግስትና አጋር አካላት 48,000,000 ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ 21,769,749 ብር (46%) ማከናወን መቻሉን ጨምረው ገልጸዋል።
በቀጣይም ህብረተሰቡ በምግብ ራሱን እንዲችልና ከተረጂነት ወደ ምርታማነት እንዲሸጋገር የተጀመሩ የተቀናጁ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተመልክቷል።
በጌታሁን ግርማ
