




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና በፕላን ዝግጅትና ትግበራ ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በቴፒ ከተማ እያካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር የማታለም ቸኮል እንደገለጹት፤መንግስት የሀገራችን ከተሞች የአፍርካ የብልጽግና ተምሳሌት እንዲሆኑ በኮሪደር ልማት ከተሞችን ለማስዋብ እና ለማዘመን ሰፊ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።
በክልሉ በከተሞች የሚስተዋሉ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን ለመፍታት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል ያሉት ኢንጂነር የማታለም፤ ከተሞች የከተማነት መስፈርት ያሟሉና ለኑሮና ለኢንቨስትመንት ምቹ እንዲሆኑ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥሉ ነው የጠቀሱት።
በከተሞች የመልካም አስተዳደር በማረጋገጥና የከተማ ልማት በማፋጠን የተሟላ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የጋራ መግባባት መፍጠር እንደሚያስፈልግም ኢንጂነር የማታለም ቸኮል ጠቁመዋል።
በዚህም በከተሞች መሠረታዊ አገልግሎት ላይ በማተኮር በተለይም የመሠረተ ልማት ዝርጋታ፣ መሬት አቅርቦት ማሳደግ እንዲሁም ከተሞችን በፕላን መምራትና የሚዘጋጁ ፕላኖችን ወደ መሬት በማውረድ ረገድ ሁሉም የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ አሳስበዋል።
በክልሉ ከተሞች ፕላን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ፀጋዬ ኃይሌ፤ የከተማ ፕላን ማዘጋጀት ከተማን የልማት አቅጣጫን ለመምራት የሚያስችል ፍኖተ ካርታና የከተማ መሬትን በአግባቡ ለማስተዳደር የሚያግዝ መሳሪያ ከመሆን ባለፈ ከተሞች ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑና የከተማ አገልግሎቶች እንዲሳለጡ አጋዥ እንደሆነም ተናግረዋል።
ከተሞች ለፕላን ዝግጅት የሚሰጡትን ያህል ለትግበራው ውጤታማነት ልዩ ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም ያስገነዘቡት አቶ ፀጋዬ ኃይሌ፤ የከተማ ፕላን ዝግጅቶችን ጥናትን መነሻ ባደረገ መልኩ ከሳይንስ ጋር አጣጥሞ በማከናወን በከተማ ልማት ሥራዎች የህዝብን ፍላጎት ማርካት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።
በከተሞች አደረጃጀትም ክልሉ ከተመሠረተ ወዲህ ባለፉት ዓመታት የከተሞች ቁጥር ከነበሩበት ከ92 ወደ 112 ማድረስ መቻሉንና በተያዘዉ በ2017 በጀት ዓመት ወደ ሥራ የገቡ ቢፍቱ፣ዋካ፣ ሸኮና ኢሰራ ባሌ ከተሞችን ጨምሮ የከተማ አስተዳደር ቁጥር ወደ 20 ማድረስ እንደተቻለም ጠቁመዋል።
በክልሉ በ2017 በጀት ዓመት የተለያዩ ደረጃ እና ዓይነት ያላቸው 44 የከተማ ፕላኖች መዘጋጀታቸውንም ጠቅሰው የቦንጋ፣ሚዛን አማን እንዲሁም የታርጫ ከተሞች ከነበሩበት ፈርጅ ደረጃ ወደ ሚቀጥለው ማደጋቸውንም አብራርተዋል።
በክልሉ የተጀመሩ ስኬቶች የተሟላ እንዲሆኑ በከተሞች ያለውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ክፍተቶችን የመመለስ ቁመናዎችን የበለጠ ማሳደግና የከተማ ልማት ሥራዎች ህዝቡን ባሳተፈ መልኩ መተግበር ይገባልም ብለዋል።
በመድረኩ የ2017 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ቀርበው የጋራ ውይይት የሚደረግ ሲሆን በፕላን ዝግጅትና ትግበራ ዙሪያ ለባለድርሻ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እንደሚሰጥም ከወጣው መረሃ ግብር ማረጋገጥ ተችሏል።
በፍቅር ከበደ
