

‹‹ጤና መድህን እጅግ ጠቃሚ መሆኑን እኔ ምስክር ነኝ›› አቶ ጥሩነህ ለሰው ልጅ፣ ዋና ጉዳዩ ጤናው ነው። ጤናው ካለ ሰርቶ መበልጸጉ፣ ተምሮም ማወቁ፣ ቀጥሎ የሚመጣ ይሆናል፡፡ ጤና ሲጓደል፣ ብዙ ጉዳዩች አብረው መጉደላቸው አይቀርም፡፡ ዓለም ምስቅልቅል ናት፣ ማግኘትና ማጣት፣ ጤናና ጤና ማጣት፣ በየቤቱ ጊዜ ጠብቀው ብቅ ይላሉ፡፡ በተለይም እንደ ካንሰር ያሉ በሽታዎች በቤተሰብ አባል ላይ ሲከሰቱ ድንጋጤን ይጭራሉ፡፡ የኢኮኖሜ አቅምን ይፈትናሉ፡፡ ከፍተኛ የህክምና አገልግሎትና ገንዘብ ይጠይቃሉ፡፡
አቶ ጥሩነህ አፈረ፣ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል፣ በካፋ ዞን ቢጣ ወረዳ ነዋሪ ናቸው፡፡ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ መተዳደሪያቸው ግብርና ነው፡፡ አቶ ጥሩነህ፣ የካንሰር ታማሚ ልጃቸውን በጅማ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ማዕከል፣ የጨረር ህክምና አገልግሎት እየተሰጠው አገኘናቸው። ልጃቸው፣ እጢ መሰል ነገር በሰውነቱ ላይ በወጣበት ጊዜ ቤተሰቡ መደናገጡ አልቀረም፡፡
አቶ ጥሩነህ ልጃቸውን በአካባቢያቸው ወደሚገኘው ሆስፒታል ፈጥነው ይዘው ለመሄድ ወደኋላ አላሉም፡፡ የአካባቢያቸው ሆስፒታል ጨና ሆስፒታል ይባላል፡፡ የጨና ሆስፒታል ሀኪሞች እና የሆስፒታሉ ማህበረሰብ፣ የአቶ ጥሩነህን ልጅ ህመም ከመለየት ጀምሮ ሆስፒታሉ አቅም እስከ ቻለ ድረስ ብርቱ ድጋፍ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ ህመሙ በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የሚታከም ሆኖ አልተገኘም፡፡
በቅብብሎሽ ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ማዕከል መምጣት የግድ ሆነ፡፡ ምርመራው በሆስፒታሉ ጠንካራ ሀኪሞች ተጀመረ፡፡ በመጨረሻም ህመሙ ካንሰር ሆኖ ተገኘ፡፡ የህመሙ ዓይነት መለየቱ መልካም ዜና ቢሆንም ‹‹ካንሰር›› መሆኑ ሲታወቅ የአቶ ጥሩነህን ቤተሰብ አስደንግጧል፡፡ ለጊዜውም ቢሆን ቤተሰቡን ዕንቅልፍ ነስቷል፡፡ ‹‹ክብር ለጅማ ዩንቨርሲቲ የህክምና ማዕከል ይሁን እና ልጄ የጨረር ህክምና እያገኘ ነው፡፡›› ይላሉ፤ አቶ ጥሩነህ፡፡
አቶ ጥሩነህን ከጭንቀት ያዳኗቸው የጅማ ዩኒቨርሲቲ የህክምና ባለሙያዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ህመም ሲመጣ ህክምና ብቻ ሳይሆን መታከሚያውም ሌላ ከባድ ጉዳይ ነበር፡፡ አቶ ጥሩነህ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባል ነበሩ፡፡ ካርድ ከማውጣት ጀምሮ፣ የአልጋ፣ የምርመራ፣ የህክምና አገልግሎት፣ የመድሀኒትና የሌሎች ወጪዎች በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተሸፍኖላቸዋል፡፡
አቶ ጥሩነህ ‹‹ጤና መድህን እጅግ ጠቃሚ መሆኑን እኔ ምስክር ነኝና ህብረተሰቡ አባል በመሆን ተጠቃሚ እንድሆን በየደረስኩበት እናገራልሁ፡፡›› ይላሉ።
መረጃው የክልሉ ጤና ቢሮ ነው
