
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመሆን በ2018 በጀት ዓመት ባለፉት ዘጠኝ ወራት የእናቶችና ሕፃናት ጤና አገልግሎት፣ የወባ በሽታ ጫና መቀነስና የጤና መድህን ተደራሽነትን በማረጋገጥ ረገድ ስኬታማ ተግባራት ማከናወኑን አስታወቀ።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም እንደገለጹት፤ በክልሉ የእናቶችንና የሕፃናትን ጤና ለመጠበቅ በተደረገው ጥረት የቅድመ ወሊድ ክትትል አገልግሎት ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል።
በዚህም 99 ሺህ 007 እናቶች አገልግሎቱን በማግኘት ከዕቅድ በላይ አፈጻጸም መመዝገቡን ገልጸዉ ከዚህም በተጨማሪ 57 ሺህ 138 (70%) እናቶች በሰለጠኑ የጤና ባለሙያዎች የታገዘ የወሊድ አገልግሎት ማግኘታቸውን አብራርተዋል።
የክልሉ ሕዝቦች የጤና ስጋት የሆነውን የወባ በሽታን ለመከላከል በተሰራው የተቀናጀ ስራ የበሽታውን ጫና ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር 50 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።
በዘጠኝ ወራት ውስጥ ለ1.4 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የወባ በሽታ የምርመራ አገልግሎት የተሰጠ ሲሆን፣ ኤች አይ ቪን (HIV) በመከላከል ረገድም የሕክምና ሽፋኑን 89 በመቶ ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
መድኃኒት ከሚወስዱ ዜጎች መካከልም የ95 በመቶው በደማቸው ያለዉ የቫይረስ መጠን በሚፈለገው ደረጃ መቀነሱን የገለጹት ኃላፊው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ለግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የደም ግፊት ልየታ ተደርጓል።
የማኅበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን (CBHI) ተደራሽነትን ለማሳደግ በተሰራው ስራ የአባላት ሽፋን 75 በመቶ የደረሰ ሲሆን፣ ከ472 ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ተሰብስቧል ነው ያሉት።
የመድኃኒት እጥረትን በዘላቂነት ለመቅረፍም በ273 ሚሊዮን ብር ግዥ ተፈጽሞ ለጤና ተቋማት እንዲሰራጭ መደረጉንም አብራርተዋል
ቢሮው የሕዝቡን ጤና ለመጠበቅ ባደረገው የቁጥጥር ስራ፣ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው ሕገ-ወጥ ምግብና መድኃኒት ከገበያ እንዲወገድ መደረጉን ጠቅሰው ባለፉት ዘጠኝ ወራትም ለ5 ሺህ 714 የጤና ባለሙያዎች የሙያ ምዝገባ የምስክር ወረቀት ተሰጥቷልም ብለዋል።
አቶ ኢብራሂም ተማም በማከልም የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠልና የታዩ ክፍተቶችን በማረም ቀሪውን የበጀት ዓመት ዕቅድ ለማሳካት የተቀናጀ ጥረት እንደሚደረግም አመላክቷል።
በፍቅር ከበደ
