
በክልሉ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ከጊዜ ወደ እየተሻሻለ በመሆኑ የክልሉን የወጭ ፍላጎት በገቢ ለመሸፈን ታልሞ እየተሰራ መሆኑን ወይዘሮ ህይወት አሰግድ ገለፁ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ከ8 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ነው የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ህይወት አሰግድ የገለፁ።
በክልሉ ከተገኘው ገቢ ውስጥ ከ7 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ የሚሆነው ከመደበኛ ገቢ እንዲሁም ከ671 ሚሊየን ብር በላይ ከማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ የተሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተገኘው ገቢ የዕዱን 90ነጥብ 76 በመቶ መሆኑን አንስተው፥ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ3.83 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አለው ብለዋል
በክልሉ ገቢን የመሰብሰብ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ያብራሩት ወይዘሮ ህይወት በክልሉ በ2014 የነበረው ዓመታዊ ገቢ 3.01 ቢሊዮን ብር ብቻ እንደነበረ ገልፀው በ2018 በግማሽ በጀት ዓመት ብቻ ከ8.358 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ገልፀዋል።
በሚሰበሰበው ገቢ ልክ የክልሉን መንግስት ወጭ በገቢ ለመሸፈን ግብ ተጥሎ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። በ2018 በጀት ዓመት መጨረሻ 64%የሚሆነውን የክልሉ መንግስት ወጪ በክልሉ ገቢ ለመሸፈን ግብ መጣሉን ገልፀው ይህ ድርሻ በ2014 ከነበረው 33.3% ጋር ስነፃፀር ከፍተኛ ለውጥ ማሳየቱን ነው የጠቆሙት።
የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ እንዳሉት ቢሮው ላለፉት ስድስት ወራት የክልሉ ኢኮኖሚ ከሚያመነጨው ሀብት መሰረት ገቢን አሟጦ ለመሰብሰብ የገቢ መሰረቶች ጥናት፥የምጣኔ ተመን ማሻሻያና የተለያዩ የህግ ማዕቀፎችን መዘርጋትና የግንዛቤ ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ ውጤቾች እየተመዘገቡ ይገኛሉ ብለዋል።
በክልሉ የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማዘጋጀት በተከታታይነት ሲሰራ ቆይቷል ያሉት ሀላፊዋ በ6 ወር ውስጥ ከ28,254 በላይ ግብር ከፋዮች በተለያዩ መንገዶች የግንዛቤ ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
ከተለያዩ ተቋማት ጋር ያለውን ቅንጅት ለማጠናከር ከ6 በላይ የተለያዩ ክልላዊ ተቋማት ጋር የጋራ ግንዛቤ ተፈጥሮ የውል ስምምነት መፈረሙን አክለው ገልፀዋል።
ግብር ስወራ፥ ማጭበርበርና ሀሰተኛ ሰነድ አጠቃቀም ለዘርፉ ፈተና ሆኖ መቆየቱን ያብራሩት ወይዘሮ ህይወት ቢሮው የታክስ ህግ ተገዥነት የበላይነትን የማረጋገጥ ተልዕኮውን እየተወጣ ይገኛል ብለዋል። በዚህም በ6ወር ውስጥ 323 ፋይል ኦዲት ተደርገው ከ132 ሚሊዮን ብር ያልተከፈለ ገቢ ግኝት መገኘቱን ጠቁመዋል። ከዚህም ከ55,435,167 ብር በላይ ወደ መንግስት ገቢ መደረጉን ጠቁመው ቀሪው በህደት ላይ ይገኛል ብለዋል።
የደረሰኝ ክትትልና ቁጥጥር በማጠናከር ለህግ ተገጂ ያልሆኑትን ለይቶ እርምጃ መውሰዱን ገልፀው በዚህም በ171 ግብር ከፋዮች ደረሰኝ ባለሙቁረጣቸው በተወሰደው እርምጃ ከ14.95 ሚሊዮን ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ መደረጉን ገልፀዋል።
ማጭበርበር ስወራና ሀሰተኛ ሰነዶችን ለመከላከል በቴክኖሎጂ የተደገፈ የግብር አሰባስበን ማጠናከር ትኩረት መደረጉን ያብራሩት የቢሮው ሀላፊዋ ወይዘሮ ህይወት አሰግድ QR ያለው የግብር ካርኒ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን ጠቁመዋል።
ግብር ለሀገር ልማትና ብልፅግና ያለውን አስተዋጽኦ ዜጎች እየተገነቡ በመምጣታቸው የታማኝ ግብር ከፋዮች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ያብራሩት ሀላፊዋ በ2017 አፈፃፀም መነሻ መሰረት በተደረገው የታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና ከክልሉ 79 ግብር ከፋዮች እውቅና አግኝተዋል ብለዋል። ክልሉ ለታማኝ ግብር ከፋዮች እውቅና መስጠት በጀመረበት በ2015 እውቅና ያገኙ ታማኝ ግብር ከፋዮች 15 ብቻ እንደነበሩ ገልፀው አሁን የታየው ከፍተኛ ለውጥ ዜጎች ለሀገራቸው ያለው ፍቅርና ታማኝነት እያደገ መምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል።
መንግስት ለታማኝ ግብር ከፋዮች ልዩ ማበረታቻ መጀመሩን በመጠቆም በዚህም 10 ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮች የታማኝ ግብር ከፋይ ልዩ መታወቂያ ካርድ በመስጠት በክልሉ በየትኛውም የመንግስት ተቋማት ውስጥ በቅድሚያ አገልግሎት እንድያገኙ የሚያስችል ዕድል ተመቻችተዋል ብለዋል። ሌሎችም በየደረጃው የመንግስት ማበረታቻዎችን እያገኙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በክልሉ የተጀመረውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ዳር ለማድረስ የገቢ ስራን በባለቤትነት ስሜት መደገፍ እንደሚገባ የጠየቁት ወይዘሮ ህይወት በጀት ዓመቱ የታዩ ክፍተቶችን በመለየት የቀሪ ወራት ዕቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት ይሰራልም ነው ያሉት፡፡
በንጉሴ ወልደየስ
