በክልሉ ዓለምአቀፍ የህጻናት ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች ተከበረ

Spread the love

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ 35ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ “ህፃናት የሚሉት አላቸው እናዳምጣቸዉ !” በሚል መሪ ቃል ዓለም አቀፍ የህፃናት ቀን በተለያዩ ዝግጅቶች በቦንጋ ከተማ ተከብሯል።

የህጻናት መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ተጠናከሮ መቀጠል እንዳለበት የገለጹት የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ገነት መኩሪያ በክልሉ የህጻናትን መብት፣ ደህነነት፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላት በማሳተፍ በርካታ ተግባራት መከናወኑን ተናግረዋል።

አለምአቀፍ የህጻናት ቀን በክልሉ በየደረጃው ባሉ መዋቅር እየተከበረ የመጣ እንደነበረ የገለጹት ኃላፊው በዚህም ተጋላጭ ህጻናትን ለመደገፍ ከ321 ሽህ ብር በላይ ሀብት ተሰብስቦ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

ቢሮው የህጻናት መብትና ደህንነት በተሟላ መልኩ ለማረጋገጥ የባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ሁሉን አቀፍ ድጋፍና እንክብካቤ እንዳያገኙ በርካታ ተግባራት እየተከናወነ እንደሆነ በመግለጽ 24ሺህ 55 በተለያዩ ምክንያቶች ከትምህርት ገበታ ውጪ የነበሩ ህጻናትን ዳግም ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

በተለያየ ምክንያት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑ ህጻናትን ወደ ትምህርት ገበታ የመመለሱ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያሳሰቡት የክልሉ የህጻናት ፓርላማ አፌ-ጉባኤ ተማሪ አቅለሲያ ባሳ የህጻናት ፓርላማው ውጤታማ እንዲሆን የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የርዕሰ መስተዳድሩ ልዩ አማካሪ አቶ ንጉስ ወ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው መንግሥት ለህጻናት ጉዳይ ትኩረት በመስጠት ማህበራዊ ብልጽግናና ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ በመግለጽ በህጻናት የሚሰሩ የፈጠራ ስራዎች አበረታች በመሆናቸው በየደረጃው ድጋፍ የሚሻ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

ከህጻናት መብትና ተጠቃሚነት አኳያ የሚነሱ ጥያቄዎችን የክልሉ መንግሥት አቅም በፈቀደው ሁሉ ለመፍታት ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ የገለጹት አቶ ንጉስ ህጻናት በትምህርታቸው በርትተው ውጤታማ መሆን እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

በመድረኩ ከክልሉ የሁሉም ዞን የመዋቅሩ አመራሮች፣ የህጻናት ፓርላማ አባላትና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን የተለያዩ አስተማሪ ዝግጅቶች እንዲሁም በህጻናት የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች ኢግዚቢሽንም ቀርቧል።

ቀኑን በማስመልከት ለተጋላጭ ህጻናት የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል።

በዕድገቱ በዛብህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *