የብልፅግና ፓርቲ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የሚያደርገውን የይምረጡኝ ቅስቀሳ በቴፒ ከተማ አስተዳደር ስር በሚገኙ ሦስቱም ቀበሌዎች በደማቅ ሁኔታ አካሂዷል።

Spread the love

በዕለቱም የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የለውጥ ዓመታቱን የልማትና የመልካም አስተዳደር ስኬቶች የሚያወሱ መልዕክቶችን በማስተጋባት በህብረት ቀበሌ፣በሰላም እና በአንድነት ቀበሌዎች ታላቅ የአደባባይ ቅስቀሳ አካሂደዋል ።

​በሰላም ቀበሌ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የቴፒ ከተማ ከንቲባ አቶ ገላቲያስ ሻሜ፤ ፓርቲው ሀገሪቱን መምራት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አመርቂ ድሎች በሁሉም ዘርፍ ተከናውኗል ብለዋል።

በተለይም በቴፒ ከተማ የነበረውን የፀጥታ ችግር በመፍታት የተሟላ ሰላም ሰፍኖ የህዝቦች ትብብር ጎልቶ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ እንገኛለን ብለዋል ከንቲባው።

በመሆኑም የተጀመሩ የልማት ስራዎችን ለማስቀጠል ነዋሪዎች የፓርቲውን የመወዳደሪያ ምልክት የሆነውን የ”ስንዴ ነዶን” እንዲመርጡ ጠይቀዋል ።

የስንዴ ነዶ የትብብር ፣የአንድነትና የሉዓላዊነት መገለጫ ስለመሆኑ በመጠቆም ዘላቂ ልማት የሚመዘግብባት ቴፒ ከተማን እንገነባለን ስሉም አክለዋል ።

​የሸካ ዞን ሥራና ክህሎት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሪት ካህኔ ገመዳ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የተገኘው ሰላም የፓርቲው ጥረትና የማህበረሰቡ ተሳትፎ ውጤት መሆኑን ገልጸዋል።

ቴፒን ከሌሎች ከተሞች ጋር ተወዳዳሪ ለማድረግና የተገኘውን ሰላምና ልማት ዘላቂ ለማድረግ ህዝቡ ከመንግስት ጎን እንዲቆም አሳስበው የተጀመሩ የልማት ስራዎች ከዳር እንዲደርሱ ብልፅግናን እንዲመርጡ ጠይቀዋል ።

​ኃላፊዋ አክለውም፣ የከተማዋን ገፅታ የሚቀይረውና በቅርቡ በይፋ ወደ ተግባር የሚገባው የአስፓልት መንገድ ግንባታ ለከተማዋ እድገት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በመጥቀስ፤ ነዋሪዎች ለልማቱ ስኬታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸዉን የዞኑ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *