



የክልሉ ግብርና ቢሮ በበኩሉ ክልሉ ማዕከሉን ከመዘጋት ታድጎ ለተሻለ ውጤታማነት ማብቃቱን አስታውቋል።
ከ3 አሰርት ዓመታት በላይ በዶሮ እርባታ ዘርፍ ለበርካቶች ዶሮና እንቁላል ሲያሰራጭ የነበረው የቦንጋ ዶሮ እርባታ ማዕከል በመሃሉ ባጋጠመው የአስተዳደር እና መሰል ችግሮች ለመዘጋት ደርሶ እንደነበር የማዕከሉ ስራ አስኪያጅ አቶ ለገሠ ሻሮ ተናግረዋል።
ሆኖም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተዋቀረ ወዲህ ለማዕከሉ በሰጠው ልዩ ትኩረትና ድጋፍ ማዕከሉ ዛሬ በተሻለ ደረጃ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ለገሠ በአሁኑ ሰዓት 12 ሺህ ቴትራ የተሰኙ ዶሮዎችን በማስገባት እንቁላል የማስጣል ደረጃ ማድረሱን ገልጸዋል።
ዶሮዎቹ በሽታ ከመቋቋምና ቶሎ ከማደግ ባሻገር ለእንቁላል እና ለስጋ የሚሆኑ መሆናቸው ከሌሎች የዶሮ ዝሪያዎች ለየት ያደርጋቸዋል ብለዋል።
ዶሮዎቹ በአሁኑ ሰዓት የምስራች እንቁላል መጣል እንደጀመሩ የጠቀሱት አቶ ለገሠ በሙሉ አቅማቸው መጣል ሲጀምሩ በቀን እስከ 7ሺህ እንቁላል ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።
ይህም በክልሉ በእንቁላል ላይ የሚታየውን የዋጋ መናር ለመታደግ የሚያስችል ከመሆኑም ባሻገር ማዕከሉ የዶሮ ጫጩት እና መኖ በተመጣጣኝ ዋጋ ለክልሉ ሁሉም ዞኖችና አጎራባች ክልሎች ለማሰራጨት ያስችለዋልም ሲሉ ገልጸዋል።
ለዚህም ማዕከሉ በአሁኑ ሰዓት በመኖ ማቀነባበሪያም ሆነ በዶሮ ጫጩት ማስፈልፈል አቅም የተሻለ ደረጃ ላይ ከመሆኑም ባሻገር የዞኖችን ፍላጎት በመረከብ ላይ በመሆኑ በቅርቡ የጫጩት ማሰራጨት ስራ ለማስጀመር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት አጠናቋል ብለዋል።
በመሆኑም በተመጣጣኝ ዋጋ የአንድ ቀን ጫጩት፣ የለማ እንቁላል፣ መኖና ክትባት ለሚፈልጉ ዞኖችም ሆነ ለግል ፈላጊዎች ምቹ አጋጣሚዎች የተመቻቹ በመሆናቸው ዕድሉን መጠቀም እንደሚችሉም አቶ ለገሠ ጥሪ አቅርበዋል።
የቦንጋ ዶሮ እርባታ ማዕከል በቀድሞ ደቡብ ክልል አዋጭ አይደለም በመባል ለመዘጋት ደርሶ እንደነበር የገለጹት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል እና የእንስሳት እና አሳ ሀብት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ታመነ በቀለ ዛሬ ማዕከሉን አዲሱ ክልል ታድጎታል ብለዋል።
በዚህም ክልሉ ለማዕከሉ በሰጠው ትኩረት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ ባለ 9 አባላት ያሉትን ቦርድ በማቋቋም እና ችግሩን ከመሠረቱ በማጥናት መፍትሔ መስጠት መቻሉን ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎ ክልሉ ወደ 60 ሚሊዮን ብር በጀት በመመደብ የማዕከሉን አጥር ከማሳጠር ጀምሮ ነባር ሼዶችን ከማደስ ባለፈ አዳድስ የማስገንባት ስራ ሰርቷል ብለዋል።
ከዚህም ባሻገር በሰዓት 30 ኩንታል መኖ ማቀነባበር የሚችል ማሽን በ5 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ከማስገባትም በላይ የማዕከሉን ጫጩት የማስፈልፈል አቅም አሁን ካለበት ከ12 ሺህ ብዙም የማይዘለውን በአንዴ ወደ 76 ሺህ ጫጩት ለማስፈልፈል የሚያሰችል ማሽን በቅርቡ እንደሚገጠም ገልጸዋል።
በመሆኑም በዚህ ማሽን በዓመት እስከ 1 ነጥብ 7 ሚሊየን ጫጩት መስፈልፈል ይቻላል ያሉት አቶ ታመነ ከዚህ የሚወጣውን ጫጩት ወደየዞኑና አጎራባች ክልሎች ለማጓጓዝ የሚያስችል ትራንስፖርት ያስፈልጋል ብለዋል።
ለዚህም የማዕከሉ አመራር ቦርድ አቅዶ እየሠራ በመሆኑ ከፌዴራል መንግስት፣ ከኤልፎራና በክልሉ መንግስት ትብብር ምላሽ እንደሚያገኝ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ከማዕከሉ የሚወጡ ጫጩቶችን በመውሰድ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሁሉም ዞኖችና አጎራባች ክልሎች መዘጋጀት እንንዳለባቸውም አቶ ታመነ ጥሪ አስተላልፈዋል ሲል የደቡብ ምዕራብ ሚዲያ ኔትወርክ ዘግቧል።
