




የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የ2017 በጀት ዓመት የ10 ወራት የገቢ አሰባሰብ የምክክር መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር አድርጓል ።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ክልሉ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ገቢን በመሰብሰብ ህብረተሰቡ የሚጠይቀውን የልማት ጥያቄ መመለስ ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የግብር ስወራንና የገቢ ማጭበርበርን ለመከላከል በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
በዚህም ውጤታማ ለመሆን የተቋማትን የሰው ሀይል በአዳዲስ አሰራሮችና በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ አቅማቸውን ማጎልበት ይገባልም ብለዋል።
የክልሉን የገቢ አቅም ለማሳደግ በንግዱ ማህበረሰብ የደረጃ ለውጥ የሚያስፈልጋቸውን በመለየት በተገቢው ሊሰራበት እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል ።
በግል ተቋማት ከሚሰሩ ሰራተኞች ተገቢውን የጡረታ መዋጮና የስራ ግብር በመሰብሰብ ማህበራዊ ዋስትናቸውን ማረጋገጥም እንደሚገባ ተናግረዋል ።
የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግድ በበኩላቸውም ከድህነትና ከተረጂነት ለመላቀቅ ከለውጡ ወዲህ የተለያዩ ማሻሻያዎችን በማድረግ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ሀብት በአግባቡ ገቢ ለመሰብሰብ ጥረቶች መደረጋቸውን ተናግረዋል ።
በዘንድሮው በጀት ዓመት በክልሉ 10 ወራቶች ከመደበኛና ከማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት 8.5 ቢሊዮን ለመሰብሰብ ታቅዶ 7.9 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 93 ከመቶ መሸፈን መቻሉን ተናግረዋል ።
በየደረጃው ያለ የገቢ አሰባሰብ እና አጠቃቀም ክፍተት ያለበት እና የግዴታ ወጪዎችን ቅድሚያ የሰጠ ባለመሆኑ ክፍተቶችን በማረም የሚሰበሰበውን ገቢ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ማድረግ ይጠበቅብናል ብለዋል ።
በምክክር መድረኩ የ10 ወራት የገቢ አሰባሰብ ሪፖርትና የገቢ አሰባሰብ አስተዳደርና አጠቃቀም ደንብ ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል።
በክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊና የታክስ ኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት አቶ ወንዱ ታደሰ የገቢ አሰባሰብ አስተዳደርና አጠቃቀም ደንብቁጥር46/2017 ላይ ገለጻ አድርገዋል።
በመድረኩም ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾን ጨምሮ የክል አመራሮች፣ የዞን፣ የከተማ አስተዳደርና የወረዳ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
በታጠቅ አበበ
