የሌማት ትሩፋት የዜጎችን ሥርዓተ-ምግብ በማሻሻል የተረጋጋ የገበያ አቅርቦት መፍጠር አስችሏል – ግብርና ሚኒስቴር

Spread the love

የሌማት ትሩፋት የዜጎችን ሥርዓተ-ምግብ በማሻሻል የተረጋጋ የገበያ አቅርቦትና ፍላጎትን በመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝ ግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

ኢትዮጵያም በተደጋጋሚ በሚያጋጥሟት የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት በርካታ ዜጎቿ ለችግር ይዳረጉ እንደነበር ይታወቃል።

ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የተለያዩ ኢኒሼቲፎች ተቀርጸው ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ።

ከዚህ ውስጥም የሌማት ትሩፋት መርኃ-ግብር አንዱ ሲሆን ዓላማውም የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥና ክብርን ማስጠበቅ ነው።

መርኃ-ግብሩ የኢትዮጵያን ደካማ የአምራችነት ታሪክ በመቀየር የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና የኢኮኖሚ እድገትን የማፋጠን ግብ የሰነቀ ሲሆን፤ በጥቂት ዓመታት ውስጥም የሚታዩና ዓለም የመሰከረላቸው ውጤቶች መታየት ጀምረዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የሌማት ትሩፋት ተነሳሽነት የዜጎችን ሥርዓተ-ምግብ በማሻሻል የተረጋጋ የገበያ አቅርቦትና ፍላጎትን በመፍጠር ጉልህ ፋይዳ እያበረከተ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከሁለት ዓመታት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት በአርባ ምንጭ ከተማ ተግባራዊ የተደረገው የሌማት ትሩፋት ለእንስሳትና ዓሳ ኃብት ምርታማነት መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ገልፀዋል።

መንግሥት ለዘርፉ ዕድገት በሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑንም አብራርተዋል።

በተለይም የእንስሳት ዝርያን በማሻሻል፣ በመኖ አቅርቦት፣ ዘመናዊ የንብ ቀፎ፣ የዶሮና የዓሳ ጫጩት ሥርጭትን በማሳለጥ በዘርፉ ላይ እመርታዊ ለውጥ መምጣቱን አንስተዋል።

ለአብነትም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሌማት ትሩፋት ተነሳሽነት ይፋ ከመደረጉ በፊት በዝርያ ማሻሻል ይዳቀል የነበረውን 500 ሺህ ላምና ጊደሮች ባለፈው ዓመት 2 ነጥብ 4 ሚሊየን በማድረስ ዕድገት መመዝገቡን ገልፀዋል።

በዚህም ከላሞች ይገኝ የነበረውን የ5 ነጥብ 8 ቢሊየን ሊትር የወተት ምርት ወደ 10 ቢሊየን ሊትር ወተት ማግኘት የተቻለበት መሆኑንም አብራርተዋል።

አርሶና አርብቶ አደሩ የአንድ ቀን ጫጩቶችን እንዲያገኝ በማስቻል በተደረገው ስኬታማ የሥርጭት ሥራም በሥጋ ዶሮና በእንቁላል ምርታማነት ላይ የሚታይ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል።

በዶሮና እንቁላል ምርት የገበያ አቅርቦትና ፍላጎት ላይ የተሻለ እንዲሆን ማስቻሉን ገልፀዋል።

የጤና መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አንድ ሰው ካርቦሃይድሬት፣ ፕሮቲንና ቫይታሚን የመሳሰሉትን ንጥረ ነገሮች የያዙ የምግብ ተዋጽዖ ውጤቶችን መመገብ እንዳለበት ያሳውቃል።

በዚህም ለሌማት ትሩፋት ተነሳሽነት በተሰጠው ትኩረት አርሶና አርብቶ አደሩን በቤተሰብ ደረጃ የአመጋገብ ሥርዓቱን በማሻሻል የተረጋጋ የገበያ አቅርቦትና ፍላጎት እንዲፈጠር ማድረጉንም ገልፀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *