በየአካባቢው የሚገኙ ሀብቶችን በተገቢው በመጠቀም ምርታማነትን ለማጎልበት በትጋት እየተሰራ እንደሚገኝ

Spread the love

ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው አስታወቁ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የተመራው ቡድን በዳውሮ ዞን ኢሠራ ወረዳ የበጋ መስኖ ስንዴ ምርት ጉብኝት አካሂዷል።

በጉብኝቱ ወቅት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት በክልሉ ምርታማትን ለማጎልበት የሚያስችሉ በርካታ ተፈጥሯዊ ሀብቶች እና አማራጮች አሉ።

በተለይም የውሃ ሀብቶችን በተገቢው በመጠቀም እንደ ክልል ከ5 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ የማልማት ተግባር እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።

አርሶ አደሩ የጀመሯቸው የመስኖ ልማት ሥራዎች ይበልጥ እንዲሰፋፉ እና ባህል ሆኖ እንዲቀጥሉ ማሳን መሠረት ያደረገ የድጋፍና ክትትል ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አብራርተዋል።

በበልግ ወቅት የታቀዱ የግብርና ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ከክልል እስከ ቀበሌ መዋቅር ምክክር ተደርጎ መግባባት ላይ ተደርሶ ወደ ተግባር መገባቱንም አስረድተዋል።

ለምርት ዘመኑ ከ 1 መቶ 50 ሺህ ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ እና ከ45 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ቀርቦ ስርጭት መጀመሩንም ጠቁመዋል።

አሁን ላይ እየተስተዋለ ያለውን ምቹ የአየር ሁኔታን በተገቢው በመጠቀም በምርት ዘመኑ የታቀደውን ዕቅድ ለማሳካት ርብርብ ልደረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ በበኩላቸው አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቅቆ ምርታማነትን እንዲያሳድግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

በየአካባቢው የሚገኙ ፀጋዎችን በተገቢው መጠቀም ከተቻለ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በኢሠራ ወረዳ የአሩሲ አንገላ ቀበሌ አርሶ አደሮች ተሞክሮ ማሳያ ነውም ብለዋል።

እንደ ዞን ከ 3 ሺህ ሄክታር የሚልቅ መሬት በመስኖ ለማልማት እንደሚቻል መለየቱን የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው አሁን ላይ ወደ 16 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በበጋ ወራት ማልማት ተችሏል ብለዋል።

ተግባሩ የአርሶአደሩን ነባራዊ የግብርናን ሥራ የቀየረ እና ተጨባጭ ውጤት የታየበት በመሆኑ በቀጣይ ጊዜያትም ትኩረት ይሰጠዋል ብለዋል።

በኢሠራ ወረዳ የአሩሲ አንገላ ቀበሌ አርሶ አደሮችም በመንግስት የተገነባላቸውን የጋሹሜ መስኖ ተጠቅመው በ216 ሄክታር መሬት ያለሙትን የስንዴ ምርቱን እያሰባሰቡ ይገኛሉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *