



የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የ2018 በጀት ዓመት አንደኛ ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ማጠቃለያ መድረክ በቦንጋ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አንድነት አሸናፊ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ በየደረጃው ካሉት የባለድርሻ አካላት ጋር በተሰራው ስራ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል ።
በዚሁም በየአካባቢው ፖሊስ የተሟላ ቁመና በመያዝ የወንጀል መከላከያ አደረጃጀት ተጠቅሞ ከመከላከል አኳያ ባለፈው ዓመት ውጤት ያመጣ ቢሆንም አደረጃጀቶቹ ወደተሟላና ወጥ ወደሆነ ቁመና ከማምጣት፤ ወንጀልን የሚጸየፍ ማህበረሰብ ለመፍጠር ጠንክሮ ከመሥራት አንጻር ውስንነት መኖሩን በመጥቀስ ካለፈው ጊዜ የላቀ ተግባር ለመፈጸም መስራት ይገባል ብለዋል።
በትራፍክ ደህንነት ዘርፍ የሚከሰት አደጋ እየጨመሩ መምጣቱን በመጥቀስ ባለፈው ሩብ ዓመት የመጣውን ለውጥ ለማስቀጠል በቁርጠኞነት መስራት፤ በዘርፉ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን በማረም አደጋውን ለመቀነስ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል ።
በመሆኑም ባለፉት ወራት የተመዘገቡ ውጤቶችን ማስቀጠልና ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት በዘርፉ እምርታ በማስመዝገብ ለህዝብ ውግንናን ማረጋገጥ እንደሚገባ አቶ አንድነት ተናግረዋል።
በምርመራ ዘርፍ የአቅም የዲስፕሊን እና የአመለካከት ጉዳዮችን በጥልቀት በማየት ከህዝብና ከመንግሥት የተሰጠውን ተልዕኮ መወጣት፣ ለቀጣይ ተልዕኮ ዝግጁ መሆን እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል ።
የምርመራ ኢንተለጀንስ ለወንጀል መከላከልም ሆነ ለምርመራ ስራ ወሳኝ ቢሆንም ባለፉት ዓመታት ጉድለቶች የታየበት በመሆኑ በማጠናከር ለምርመራ ውጤታማነትና ለህግ በላይነት መረጋገጥ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል።
የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሸን ኮሚሽነር ዶክተር ካሣ ኮሚሸኑ ባለፈው ሦስት ወራት ሲያከናውን የነበረውን አፈጻጸሙን በመገምገም ጥንካሬን ለማስቀጠልና ጉድለቶችን ለማረም ያለመ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የፖሊስ ቁመና እና አመለካከትን የተሻለ ለማድረግ ሲያካሄድ የቆየውን የግምገማ ውጤት የሚታይበት በመሆኑ ተሳታፊዎች በጥልቀት እንዲወያዩ አሳስበዋል።
የየዞኑ ፖሊስ ምሪያ የ1ኛ ሩብ ዓመት ሪፖርት ለተሳታፊዎቹ በመምሪያው አዛዦች እየቀረበ ይገኛል።
በጌታሁን ግርማ
