የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?

Spread the love

ባለፉት ተከታታይ ወራት ‘’የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልልን ምን ያህል ያውቃሉ?’’ በሚል አምድ አጠቃላይ የክልሉን ገጽታ የሚያሳዩ እና የስድስቱ ዞኖች የተለያዩ ባህላዊ ይዘቶችን የዳሰሱ ጽሁፎችን  ለውድ አንባቢያን አጋርተናል፡፡ 

በተመሳሳይ ሁኔታ ዛሬ በዚሁ አምድ ”‎የደቡብ ምዕራብ ኢትጵያን ምን ያህል ያውቃሉ? በሚለው ፕሮግራማችን “ፀቱዋ”(የዳዉሮ ማህበረሰብ የቀንድ ከብት ቆጠራ ሥርዓት) አንቃኛለን አባራችሁን ሁኑ፡፡

ፀቱዋየዳውሮ ማህበረሰብ የቀንድ ከብት ቆጠራ ሥርዓት

የዳውሮ ብሔር የራሱ የሆነ የተለያዩ ባህል ወግና እሴት ያለዉ ማህበረሰብ ነዉ፡፡አብዛኛዉ ማህበረሰብ የኢኮኖሚ መሠረቱ የግብርና ስራ ላይ የተመሰረተ ሲሆን በዋናነት በከብት እርባታ፤በሰብል ልማትና በንግድ ስራም ይታወቃል፡፡ ከእነዚህ የኢኮኖሚ መሰረቶች መካከል በዳውሮዎች ዘንድ በከፍተኛ የገቢ ምንጭነት የሚታወቅው የእንሰሳት እርባታ ስራ ነዉ፡፡ከብት እርባታ በማህበረሰቡ ዘንድ ትኩረት ከመሰጠቱም ባሻገር በዘርፉ የሀብት መጠንና የአርቢን ጥንካሬ ለማየት በዳዉሮ ማህበረሰብ ዉስጥ እንሰሳት ቆጠራ (ፀቱዋ) ስርዓት ይከናወናል፡፡

ረጃጅም ቀንድ ያላቸዉ እና በወተት አሰጣጥ…

የዳውሮ ብሔር ኢኮኖሚ መሰረት ከሆኑት የእንሰሳት እርባታ ዉስጥ አንዱ የቀንድ ከብት እርባታ ነው፡፡በማህበረሰቡ ዘንድ ተመራጭ የሆኑ የእንሰሳት ዝሪያዎች አሉ፡፡ከነዚህም ዉስጥ በቀንዳቸው እጀግ ግዙፍና በወተት አሰጣጥ የሚታወቁት ቦብያ/ቡልኪያ/ በመባል ይታወቃሉ፡፡ልዩ ስማቸው ቦብያ/ቡልኪያ/ከብቶች ዝርያ በመባል ይታወቃሉ፡፡ ከዚህ ዝርያ ሌላ ደግሞ ዱማሷዋ ተብለው የሚታወቁም አሉ፡፡ በዳዉሮ ማህበረሰብ ዘንድ የቀንድ ከብት ሀብት ልማት ለመጀመር በቅድሚያ ከትንሽ ነገር ይነሳል፡፡ይህ ማለት አንድ ሰው መጀመሪያ ከብት እንዲኖረው ቀደም ብለው የገቢ ማግኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ዶሮን ከዶሮ ወደ ፍየልና በግ በማሳደግ ከፍየልና ከበግ ጠርቀም ያለ ገንዘብ በማግኘት ከብትን ይገዛል፡፡

በዚህም ሂደት ሀብት የሌለው ሰው ሀብት መጀመሪያ የማግኛ ሂደት ሚዛ ዴኡዋ ተብሎ ይጠራል፡፡ በዳወሮዎቹ ዘንድ ለአንድ ሰዉ ብዙ ከብቶችን ማፍራት በጣም ዝናና እውቅና የሚያሰጥ፤የሚያስከብር እና ታዋቂ ሀብታም የሚያስደርግ ተግባር ነው፡፡

በዚህም ሂደት የብዙ ቀንድ ከብቶች ባለቤት የሆነ ሰው በማህረሰቡ ሀብታም ተብሎ የሚከብር፣ ለድሆች ለማርባትና በጋራ ለመጠቀም ጥያቄ ስያቀርቡ የሚያካፍል የተባረከና ምስጉን የሚባል ለፈጣሪ  ታማኝ ተብሎ የሰውን ሀብት ጥበቃ አደራ ጭምር የሚሰጥ ሰው ይሆናል፡፡ ግለሰቡ የበርካታ የቀንድ ከብቶች ባለቤት ለመሆን በየትኛውም የሀብት አሰባሰብና ገንዘብ ማግኛ ጉዳይ ላይ በማህረሰቡ ዘንድ በቁጠባ የሚታወቅ፤ሀብት የማያባክን፤ክፉ ነገር የማይሰራ፤ትንንሽ የሀብት መፍጠሪያ መንገዶችንም ሳይንቅ ከትንሽ ወደ ትልቅ ኢኮኖሚ የሚገሰግስ ሰው ተብሎም ይታሰባል፡፡በዚህ ዘርፍ ከፍተኛ ደረጃ የደረሰ ግለሰብ የጸቱዋ(የከብት ቆጠራ) ስርዓት ይከዉናል፡፡

    ፀቱዋ-የከብት ቆጠራ ስርዓት

ፀቱዋ ማለት አንድ የቀንድ ከብት አርቢ የሆነ ግለሰብ ወይም አርሶ-አደር በርካታ ታዛቢና ታዳሚ የሆኑ ጓዳኞች፤ዘመዶች እና ጎርበቶች ባሉበት የከብት ቆጠራ ቀንን በመወሰንና ታላቅና የከበረ ድግስ በማዘጋጀት የቀንድ ከብቶችን በገመድ ቆጥሮ አንድ መቶ በማሙላት ከማህበሰቡ ዘንድ የባለሀብትነት ዝናንና ዕውቅናን የሚያገኝበት ሀገር በቀል የሀብት አሰባሰብ እና ቆጠራ ሥርዓት ነው፡፡

ባለሀብቱ የቆጠራ ስርዓት ከዋኞችን በራሱ በጎ ፍቃድ የቅርብ ጓዳኛን/ዘመድን በማቅርብ እንዲቆጥሩ ያደርጋል፡፡ ከብቶች በሚደረገው ቆጠራ 100 መሙላታቸው ስረጋገጥ አንድ ጥጃን /ወይፈንን ቀለል ካለ ጉብታ በማንከባለልና ሀብት የሌለውን ሰዉ በማንሳት እንዲረከብና ሌሎቹም ከዚህ ከበራ ክውና ሂደት ጥሩ ግንዛቤ እንዲያገኙ የሀብት አሰባሰብ ዕውቀቱ ለቀጣይ ትውልድ እንዲሻጋገር የሚደርግበት ባህላዊ ሥርዓት ነው፡፡

በአሁኑ ሰዓት በዳውሮ ዞን ውስጥ ከሚገኙ ወረዳዎች በርካታ የቀንድ ከብት ባለቤት የሆኑና ስርዓቱንም አክብረው ከማህበረሰቡ ዕውቅናና ዝናን ያተረፉ ዱሪያ(ሀብታም)ተብሎ የሚታወቁ ሀገር በቀል የቀንድ ከብቶች ሀብታም የሆኑ ሰዎች አሉ፡፡ ለዚህ ባህላዊ ሥርዓት ከበራ በዓል ከተለያዩ ቦታዎች በጥሪ ለሚመጡ ተጋባዥ እንግዶች በዕለቱ እየበሉና እየጠጡ የሚዝናኑበት ነዉ፡፡የከብት እርድ ተፈፅሞ የሚዘጋጁ የባህል ምግቦች ለተጋባዥ እንግዶች እንዲዳረስ ተደርጎ በጥንቀቄ ይዘጋጃል፡፡ከሥጋ ምግቦች በተጨማሪም የወተት ተዋፅኦ እና ባህላዊ መጠጦች በበቂ ሁኔታ ተዘጋጀተው ለታዳሚዉ ይቀርባሉ፡፡ በፀቱዋ ከበራ ቀን የተሰባሰቡ አባቶች፣ዘመዶችና የቅርብ ጓዳኞቹም ሂደቱን ከተመለከቱ እና ካረጋገጡ በኋላ ለዕለቱ እንግዶች የተዘጋጀዉን ምግብና መጠጥ ከበሉና ከጠጡ በኃላ ባለሀብቱን ይሸልማሉ፤ይመርቃሉ እንዲሁም ያወድሱታል፡፡በመጨረሻም በከብቶቹና በቤተሰቦቹም ላይ ምንም ዓይነት እንከን እንዳይፈጠር እና ሀብቱም ተባርኮ እንዲያድግለት ፈጣሪን ይለማመኑለታል፡፡ ተራ በተራም ይመርቁታል፡፡

 ለባለሀብቱ ከማህበረሰቡ አባላት የሚሰጠው ክብርና ዕውቅና

ለባለሀብቱና ለቤተሰቦች ዱሪያ ኬሳ(የሀብታምነት እዉቅና የተሰጠዉ ሰዉ) ተብሎ ልዩ ስፍራ ይሰጣቸዋል፡፡ለሰውና ለፈጣሪ ታማኝ/ የተወደደ ሰው /የተባረከ ነው ይሉታል፡፡ ለጋሽ ተብሎ ይታወቃል፡፡ ማህበራዊ ዝና ይጨምርለታል፡፡ታማኝ በመሆኑ የሰውን አደራ እንዲጠብቁም ኀላፊነት ይሰጣቸዋል፡፡ሀገር በቀል የሀብት ፈለግ መምህር ይባላሉ፤ለሌሎች አርአያም ይሆናሉ፡፡

 የፀቱዋ እና ዳላ ከበራ ሥርዓት ልዩነት

ፀቱዋ የቀንድ ከብቶች ተቆጥሮ 100 ስሞላ የሚከናወን ስርዓት ሲሆን ዳላ የሚባለወ ሁለት መቶና ከዛ በላይ ቁጥር ስሞላ የሚከናወን ስርዓት ነዉ፡፡አንድ ሰዉ ከ130-150 የቀንድ ከብቶች ቁጥር ስደርሰለት ሊቁዋን ዳሌዳ ይባላል፡፡ ሁለት መቶና ከዚያ በላይ ሲሆን ደግሞ ላኡዋ ፀተዳ/laa’uwan s’eetseda/ ሙሉዋ ዳሌዳ ይባላል፡፡ከፀቱዋ/ዳላ ጋር ተያይዞ ለዕውቅና የሚነገሩ ሰነ-ቃሎችም በዳዉሮ ማህበረሰብ ዘንድ የተለመዱ ናቸዉ፡፡

 ከፀቱዋ/ዳላ ጋር ተያይዞ ለዕውቅና የሚነገሩ ሰነ-ቃሎች

ጎቺ ጎሪያዋናው ፀቲ አፎታዋናው

ኮይ ኮይ ኮዳዋናው ኮርማ ቦራዳ ኬስ ኬስ ቡራዛዋናው

ኮራ ግድ ቶጋዋናው ሙጻግድ ላጻዋናው

ዎጻ ግድ ዋይታዋናው አሳ ካሪያ ሽሻዋናው

ናአው ዋይታዋናው ማንቆ ዋጀዋናው

ደሪ አንጃዋናው ኦማቲ ካውዋናው

እየጠባለ በተለያዩ ማህበራዊ ኩነቶች የዝና ፋከራ ይፎክራሉ፡፡

የመረጃ ምንጭ፤የዳዉሮ ዞን ባህል፣ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ

   አዘጋጅ፣ካሳሁን አሰፋ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *