








ከ4 ወራት በኋላ የህዳሴ ግድብ 3 ተጨማሪ ተርባይኖች ወደ ስራ እንደሚገቡና በድምሩ 7 ተርባይኖች ኃይል ማመንጨት እንደሚጀምሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለኢቲቪ ገልጸዋል።
እስከ መጪው ታህሳስ ወር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ70 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ በላይ ውኃ መያዝ እንደሚችልም ተናግረዋል።
በታህሳስ ወር የግድቡ የሲቭል ስራ መቶ ፐርሰንት ይደርሳል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አጠቃላይ የግድቡ ስራ ደግሞ የዛሬ ዓመት ገደማ የመጠናቀቅ ምዕራፍ ላይ እንደሚደርስ ጠቁመዋል።
የአባይ ወንዝ ፍሰት ሳይስተጓጎል ከመቀጠሉም በተጨማሪ የግድቡ የውሃ ማስተንፈሻ በሮች ተከፍተው በሰከንድ 2‚800 ሜትር ኪዩብ ተጨማሪ ውሃ ማፍሰስ ጀምረዋል ብለዋል።
ውኃው ከፍ እያለ ሲሄድ ግድቡን ሞልቶት የግንባታ ስራውን እንዳያስተጓጉልብን በማሰብ የማስተፈንስ ስራ ሰርተናል ብለዋል።
በተያዘው ዓመት በጣም ከፍተኛ ዝናብ ስላለ በየቀኑ የምንይዘው የውኃ መጠን ትልቅ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ማስተንፈሻው ባይከፈት ኖሮ ግድቡ በ10፣ ቢበዛ በ15 ቀናት ውስጥ ሞልቶ መፍሰስ ይጀምር እንደነበር ጠቅሰዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ፍሰትን በመቆጣጠር፣ የጎርፍ አደጋ ስጋትን በመቀነስ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተለይ በድርቅ ዘመን መጠኑ ያልዋዠቀ የውሃ አቅርቦት እንዲደርሳቸው ያደርጋል ብለዋል።
ይህ የተመዘነና የተመጣጠነ የውሃ ልቀት ግብርናን፣ የኃይል የማመንጨት ሥራን እንዲሁም በቀጠናው ያለ የሀብት አጠቃቀም ምጣኔን ለማጎልበት በእጅጉ ይጠቅማል ነው ያሉት።
ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት በተርባይን ከምንለቅላቸው ባሻገር ያንን ያክል ተጨማሪ ውኃ የምንለቅላቸው ውኃን እታች በማሳነስ እኛ ልዩ ተጠቃሚ የመሆን ፍላጎት ቀድሞውኑ ስላልነበረን ነው ብለዋል።
ይህ ውኃ የጋራ ሀብታችን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ የኛ ኃላፊነት እንደ ሀገርና እንደ ህዝብ የሚገባንን ያህል ተጠቅመን የሚገባቸውን ያክል ለወንድሞቻችን ማካፈል ነው ሲሉ ተናግረዋል ያለው ኢቢሲ ነው።
