5ኛው የፓኪስታን-አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባኤና አውደ ርዕይ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

Spread the love

5ኛው የፓኪስታን-አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባኤና አውደ ርዕይ ከግንቦት 7 እስከ 9/2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚካሄድ በኢትዮጵያ የፓኪስታን አምባሳደር አቲፍ ሸሪፍ ሚያን ገለጹ።

አምባሳደሩ በሰጡት መግለጫ፥ በንግድ ልማት ጉባኤና አውደ ርዕዩ ላይ ከ100 በላይ የፓኪስታን አምራች ድርጅቶች ይሳተፋሉ ብለዋል።

ከአፍሪካ ሀገራት ጋር የንግድ ትስስርን የሚያጠናክሩ የሕክምና መድኃኒት ምርትና መሣሪያዎች፣ የውበትና ቆዳ እንክብካቤ ውጤቶች፣ የጨርቃጨርቅና አልባሳት ምርቶች፣ የምግብና የምግብ ነክ የግብርና ምርቶች፣ የአውቶሞቲቭ መለዋወጫዎች፣ የኤሌክትሪክና የቤት እቃዎች በአውደ ርዕዩ እንደሚቀርቡም ገልጸዋል።

በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር፥ የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የፓኪስታን ባለሃብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋያቸውን ፈሰስ እንዲያደርጉ ተነሳሽነት እየፈጠረ ነው ብለዋል።

ባለሀብቶቹ በግብርና ማቀነባበር፣ በጨርቃጨርቅ፣ በሕክምና እና ሌሎት የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሳተፉ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

5ኛው የፓኪስታን አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባኤና አውደ ርዕይ በኢትዮጵያና ፓኪስታን መካከል ያለውን ጠንካራ ትብብር የበለጠ ለማጠናከር ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው አንስተዋል።

በፓኪስታን-አፍሪካ የንግድ ልማት ጉባኤና አውደ ርዕይ የአፍሪካ ሀገራት እና የፓኪስታን መንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የንግድ መሪዎችና ባለሃብቶች የሚሳተፉ ሲሆን፥ ዝግጅቱም የንግድና ኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ መሆኑ ተገልጿል።

የንግድ ልማት ጉባኤ፣ የሁለትዮሽ የንግድ ውይይቶች፣ የመንግስት ለመንግስት የምክክር መድረኮችን ጨምሮ የተለያዩ ሁነቶች እንደሚካሄዱም ይጠበቃል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *