








የፌዴራል እና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ከወከላቸው ሕዝብ ጋር ያደረጉትን ውይይትና የመስክ ምልከታ አስመልክቶ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እና ሌሎች የክልሉ አስፈጻሚ አካላት በተገኙበት በቦንጋ ከተማ ግብረ መልስ ሰጥቷል ።
የፌደራልና ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በክልሉ በሁሉም ዞኖች በተለያዩ ወረዳዎች ከወከላቸው መራጭ ሕዝብ ጋር በሰላም፣ ልማትና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውም ተገልጿል።
ከውይይቱ ባሻገርም የልማት ሥራዎች የመስክ ምልከታ በማድረግ መጠናከር የሚገቡ እና የቀጣይ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ላይም ከመራጩ ህዝብ ጋር በመወያየት ከዞን እስከ ወረዳ ድረስ ባሉት ለሚመለከታቸው መዋቅሮች ግብረ መልስ ሰጥቷል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቶች አባላት በክልሉ መንግሥት በጀት በልማት አጋር ድርጅቶች ድጋፍና በህብረተሰብ ተሳትፎ በሰላምና ፀጥታ፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ጉዳዮች የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ሥራዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ለውጥ እያሳዬ በመሆናቸው እንዲጠናከሩም አመላክቷል።
በግንባታ ላይ ያሉ የመንገድና ድልድይ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የጤና ተቋማት፣ ቴክኒክ ሙያና ኢንዱስትሪያል ኮሌጅ፣ የመነኻሪያ ፕሮጀክት ግንባታዎች ማፋጠን የቆሙትን ወደ ሥራ ማስገባት ይጠበቃልም ተብሏል።
አሁንም የውስጥና የአጎራባች ሰላምና ፀጥታ ማስከበር፣ ኑሮ ውድነት፣ መንገድና ድልድይ ፣ጤናና ትምህርት ልማት፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ ህገወጥ ንግድ መቆጣጠርና መከላከል፣ ፍጆታ ምርት እና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ማሻሻል የሁሉም ድጋፍና ክትትል የሚፈልጉ መሆናቸውም ተብራርቷል።
የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ-ጉባዔ የተከበሩ አቶ ወንድሙ ኩርታ አባላቱ ከመራጩ ሕዝብ ጋር በሰላም፣ ልማት፣ በመልካም አስተዳደር ላይ ከመወያየት ባለፈም የመስክ ምልከታ በማድረግ መጠናከር የሚገቡ እና ትኩረት የሚሹ ጉዳዮችን በመለየት በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች ግብረ መልስ እንደተሰጠም አንስተዋል።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ በውይይቱ እንደገለጹት በክልሉ የተረጋጋና ሰላማዊ የፖለቲካ አከባቢ በመፍጠር ለዜጎችና ለኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ምቹ ሁኔታዎች እንዲኖሩ ይሰራል።
በክልሉ መሠረታዊ ችግር የሆነው የመሠረተ ልማት በተለይም መንገድና ድልድይ እንዲሁም በማህበራዊ ልማት ሥራዎች ጤናና የትምህርት ልማት የአገልግሎት አሰጣጥ ማሻሻል ቅድሚያ የሚሰጡ ጉዳዮች ናቸውም ብለዋል።
ያለውን እምቅ አቅም በመጠቀም በቀላሉ ወደ ሀብት መቀየር የሚያስችሉ የግብርና ሥራዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በእንስሳት እና እርሻ ልማት ትኩረት በመስጠት የግብርና ምርትና ምርታማነት ማሳደግና በቱሪዝምና በማዕድን ምርት ላይ ትኩረት በመስጠት ሀብት ለማካበት ትኩረት ይሰጣል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ።
ተጀምሮ ግንባታቸው የተጓተቱ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክት ግንባታዎችን ደረጃ በደረጃ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግም ያነሱት ዶክተር ነጋሽ ዋጌሾ በጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦት በማሳደግ ህገወጥ የመድሃኒት ስርቆት በመከላከልና በመቆጣጠር የአገልግሎት አሰጣጥ ለማቀላጠፍ ይሰራልም ብለዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ከህብረተሰቡ የተነሱ ጥያቄዎች ተገቢና መፍታት የሚገቡ በመሆናቸው በየደረጃው ያሉ የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
በዚህም በየተቋማት ያሉ የሰው ኃይል አቅም በመገንባትና በማብቃት እንዲሁም በተግባር ውጤታማነት የሚመዘን አመራር መፍጠር ለህዝቡ ተጠቃሚነት እንደሚሰራ ጠቁመው የክልሉ የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሥራዎችን የከተሞች አቋምና ህብረተሰቡን ትብብር በማጠናከር ማስቀጠልና ወደ ሁሉም ማስፋፋት ይጠበቃል ነው ያሉት።
ርዕሰ መስተዳድሩ ጠንካራ ብድርና ቁጣባ መዘርጋት፣በአርብቶ አደርና በከፊሌ አርብቶ አደር አካባቢዎች ዘላቂ ሰላምና ፀጥታ ማስከበርና ኑሮአቸውን በተጨባጭ የሚያሻሽል ሥራዎችን ማከናወን እንደሚጠበቅና በፌደራል መንግስት የሚሰሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ግንባታቸው የተቋረጡት ወደ ሥራ እንዲገቡ የተጀመሩ ጥረቶች ተጠናክሮ ይቀጥላሉም ብለዋል።
በፍቅር ከበደ
