በቴፒ የተከፈተው የምርት ጥራትና ሰርቲፊኬሽን ማዕከል የንግድ እንቅስቃሴውን እያቀላጠፈ መሆኑ ተገለጠ

Spread the love

በኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ስር የሚገኘው የቴፒ ምርት ጥራትና ሰርቲፊኬሽን ማዕከል አገልግሎት መጀመር በአካባቢው ለሚገኙ አምራቾች፣ ላኪዎችና ሥራ አጥ ወጣቶች ዘርፈ ብዙ ጥቅም እያስገኘ መሆኑ ተገለጠ። ማዕከሉ በተለይም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በሸካ ዞን ና በጋምቤላ ክልሎች የሚመረተው ቡና የራሱ መለያ ኖሮት ለገበያ እንዲቀርብ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ ተመላክቷል።

የቴፒ ምርት ጥራት ምርመራና ሰርተፊኬሽን ማዕከል ሥራ ከጀመረ ሁለት ወራት ተቆጥረዋል። ማዕከሉ አገልግሎት መጀመሩን ተከትሎ ቀደም ሲል ለጥራት ምርመራ ይደረጉ የነበሩ የጊዜና የወጪ እንግልቶች መቀነሳቸው ተገልጿል።

የማዕከሉ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል ሻወኖ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ማዕከሉ ለሸካ ዞን እንዲሁም ለጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን ወረዳዎች የታጠበና ያልታጠበ ቡና የጥራት ደረጃ መመደብና የብቃት ማረጋገጫ መስጠት ጀምሯል። ኃላፊው አክለውም አቅራቢዎች ምርታቸውን በወቅቱ በማስመርመር የገበያ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ማዕከሉ በዋናነት ደረጃ ይመድባል፤ ብቃት ያረጋግጣል። ትልቁ ፋይዳው ግን በአቅራቢና በላኪ መካከል ያለውን የንግድ ግልጽነት ማረጋገጡ ነው። ላኪው ለአቅራቢው ክፍያ መፈጸሙ ሳይረጋገጥ ምርቱ ከማዕከሉ አይወጣም ብለዋል አቶ ሳሙኤል ።

የማዕከሉ መከፈት ከንግድ ትስስር ባለፈ በአካባቢው ለሚገኙ ወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠሩም ተመላክቷል። በማዕከሉ የተደራጁ 78 ወጣቶች በቀጥታ ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት የማህበሩ ሰብሳቢ ወጣት ፍቅሩ ገብረመድህን፤ መንግስት በፈጠረው ምቹ ሁኔታ ወጣቶቹ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን መደገፍ መቻላቸውን ይናገራሉ።

በማዕከሉ አገልግሎት እያገኙ የሚገኙ የቡና አቅራቢዎችና የላኪ ወኪሎች በበኩላቸው፤ የአገልግሎቱ መጀመር የነበረባቸውን የቢሮክራሲና የጉዞ እንግልት እንደቀነሰላቸው ገልጸዋል።

ማዕከሉ የጋራ ሀብታችን በመሆኑ በባለቤትነት ልንጠብቀው ይገባል። አሽከርካሪዎችና ባለሀብቶች ከቤታቸው ሳይርቁ ፈጣን አገልግሎት እያገኙ ነው ስሉ የተደራጁ ወጣቶች።

ማዕከሉ የከተማዋን ገቢ ከማሳደግ ባለፈ ነጋዴዎችና ባለመኪኖች በቀላሉ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ ትልቅ ዕድል መፍጠሩ ተገልጿል ሲል የሸካ ዞን ኮሙኒኬሽን ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *