




በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መንግሥት ገቢዎች ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት የደረጃ ‘ሐ’፣’ለ’ እና ‘ሀ’ ግብር ከፋዮች የግብር ማስጀመሪያ ክልላዊ ንቅናቄ መድረክ በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በንቅናቄ መድረኩ የተገኙት ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) መንግስት ለዜጎች የሚያቀርባቸው የተለያዩ አገልግሎቶች የሚሸፈኙት ከግብርና ከታክስ ከሚገኘው ገቢ እንደሆነም ተናግረዋል።
የክልሉ የገቢ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በ2018 በጀት ዓመት 18 ቢሊዮን በላይ ብር ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ የተያዘ በመሆኑ ግብር ከፋዮች፣አመራሩ፣የግብር ባለሙያዎች እንዲሁም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።
የግብር ከፋዩ ገቢ በጨመረ ቁጥር የመንግስት ገቢ መጨመር መቻል አለበት ያሉት ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገቢ የፈጠረውን ምቹ ዕድል ለመጠቀም ገቢ አቅም ማሳደግ፣በመንግሥት እና በግብር ከፋዩ መሀል መቀራረብ ማጠናከር፣በማዕድን ዘርፍ ትኩረት ማድረግ፣የገቢ አሠራሮችን ማዘመን ይገባል ብለዋል።
ታማኝ ግብር ከፋይ እንዳሉ ሁሉ ህግን የማያከብሩ ግብር ከፋዮች ስላሉ እነዚህ አካላት የተጣለባቸውን ገቢ በወቅቱ እንዲከፍሉ ያሳሰቡት ርዕሰ መስተዳድሩ በገቢ አሰባሰብ ሥርዓቱ ላይ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግም አስረድተዋል።
የክልሉ መንግስት ወጪን በክልሉ ከሚሰበሰብ ገቢ ለመሸፈን እየተሰራ እንደሚገኝ የገለጹት የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ህይወት አሰግ፤ ክልሉ ሲመሰረት ከነበረበት 36 በመቶ የገቢ ድርሻ በ2017 በጀት ዓመት 57 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉን አስረድተዋል።
በ2017 በጀት ዓመት ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ታቅደው እስካሁን ባለፉት 11 ወራት ከ9 ነጥብ ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የጠቀሱት ወ/ሮ ህይወት በ2018 በጀት ዓመት ከ18 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የገቢ ድርሻውን 66 በመቶ በላይ ለማድረስ እንደሚሰራ ነው የገለጹት።
የቢሮ ኃላፊዋ፣ በ2018 በጀት ዓመት የላቀ ገቢ በመሰብሰብ የክልሉን መንግስት የልማት ወጪ 64% በመሸፈን የህዝቡን የልማት ፍላጎት ደረጃ በደረጃ የመመለስ ስራዉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅሰዋል።
ለ2018 በጀት ዓመት ለገቢ ዕቅድ መሳካት ክልላዊ የገቢ እምቅ አቅም ጥናት በማካሄድ የገቢ አቅም ምጣኔ መለየት፣የደረጃ ሽግግር መስራት፣በትምህርት ቤቶች የታክስ/ግብር ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ የግብርና ታክስ አሰባሰባና አስተዳደር ሥርዓትን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማስደገፍ ይሰራልም ብለዋል።
የታክስ ኦዲት ሥራ ማጠናከርና የህግ ተገዥንትን ማረጋገጥ፣የገቢ መዋቅርና ባለሙያዎች አቅም መገንባት፣የማዘጋጃ ቤታዊ ገቢ አሰባሰብና አስተዳደር ሥርዓት ማጠናከር፣ታክስ ደረሰኝ አሰጣጥ ላይ የሚስተዋለውን ማነቆ መፍታትና የሽያጭ ማሽን አጠቃቀም ሥርዓትን በማሻሻል የሂሳብ መመዝገቢያ ማሽን ተጠቃሚዎች ቁጥር የመጨመር ሥራዎች ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸውም ብለዋል።
በክልሉ ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር ስርዓት በመገንባት የ2018 የግብር ዘመን የገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ከእጅ ንክኪ በፀዳና የግብር ከፋዩን እንግልት በሚቀንስ አኳኋን በቴሌብርና በባንክ አማካኝነት እንዲፈፀም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ስራዎች የተጠናቀቀ በመሆኑ ግብር ከፋዮች የተፈጠረውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም ግብሩን በወቅቱ የመክፈል ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፍቲን በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸዉ ክልሉ ብሎም ቤንች ሸኮ ዞን ለም የእርሻ መሬት፣የግብርና ምርቶች፣የማዕድን ሀብቶችና የቱሪዝም እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ ከእነዚህ ሀብቶች ገቢውን በአግባቡ መሰብሰብና የሚሰበሰበውን ገቢ ለታለመለት ዓለማ ማዋል እንደሚገባም ተናግረዋል።
በግብር ማስጀመሪያ ክልላዊ ንቅናቄ መድረኩ የተዘጋጀውን የንቅናቄ ሰነድ በቢሮ ምክትልና የኦፕሬሽን ዘርፍ ኃላፊ በአቶ ወንዱ ታደሰ እየቀረበ የሚገኝ ሲሆን ከሚቀርበው ሰነድ መነሻ የጋራ ውይይት ይደረጋል።
በፍቅር ከበደ
