







ውይይቱ ከ2020_2025 ድረስ በክልሉ ሲተገበር የነበሩ የልማት ፕሮግራሞች እየተጠናቀቁ በመምጣታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ከተባበሩት መንግስት/ዩኒሴፍ/ ዘላቂ ልማት አጋሮች ጋር ስራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው ባደረገው ስምምነት ቀጣይ 2025-2030 ድረስ ክልሉ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የልማት አጀንዳዎች ሀሳብ አሰባስቦ በማካተት ፊዝካልና ፋይናንሻል ዕቅድ ለማቀድ ታልሞ የተዘጋጀ ነው።
የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ወሰነች ቶማስ በውይይት መድረኩ እንደገለጹ በክልሉ ባለፉት ጊዜያት በስምንት ሴክተር መ/ቤቶች በ17 ወረዳዎች የትምህርት ቁሳቁስ እጥረት ያጋጠማቸው ህፃናቶችን በመደገፍ፣ንጹህ መጠጥ ውሃ በአቅራቢያ ማግኘት ያልቻሉ እናቶችና ህፃናት ዉሃ እንዲያገኙ፣በሴቶችና ህፃናት ላይ በስርዓተ ምግብ ችግር የሚከሰተው የመቀንጨርና ሌሎች የጤና ችግሮች እንዲሁም ለአደጋ ስጋት ተጋላጭ አካባቢዎች አስቸኳይ ድጋፍ በመስጠት ረገድ ፕሮግራሙ ሰፊ ስራዎችን በማከናወኑ የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ነው ብለዋል።
ድርጅቱ በቀጣዩ አምስት ዓመታት ክልሉ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የልማት አጀንዳዎችን የስትራቴጅክ መካከለኛ ዘመን ዕቅድ አካል በማድረግ ከዚህ ቀደም ሲተገበር ከነበረው የተሻለ ሀብትና አቅም በማካበት ሰፊ የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ሙሉ እምነት እንዳላቸውም ወ/ሮ ወሰነች ገልጸዋል።
በመድረኩ የተገኙት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ እና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አልማው ዘዉዴ እንደገለጹት ድርጅቱ በትምህርት፣በጤና፣በሴቶችና ህፃናት፣ለአደጋ ስጋት ተጋላጭ በሆኑ አከባቢዎችና በሌሎች ልማት ጉዳዮች እየሰራ ያለው ተግባር የሚመሰገን ነው።
ክልል ዓቀፍ የሆነ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ አሁንም ቢሆን ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ስላሉ እንደክልል የጋራ ምክክርና ቅንጅታዊ አሰራሮችን በማጠናከር አስፈላጊ የሆኑ ድጋፎች እንደሚደረጉም አቶ አልማው ዘዉዴ አንስተዋል።
በክልሉ ባለፉት ዓመታት በ106.8 ሚሊዮን በጀት በተለያዩ ፕሮግራሞች ድርጅቱ ስራዎችን ሲሰራ መቆየቱን የጠቆሙት የዩኒሴፉ ሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሪት መስከረም ደምሴ በውይይቱ የተሰበሰበው ግብዓት የዕቅድ አካልና ለቀጣዩ ስራ አጋዥ እንደሚሆን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እንደተጠበቁ ሆኖ 2025-2030 ድረስ በክልሉ ቅድሚያ በሚሰጣቸው የመጀመሪያ ደረጃ የጤና ተቋማት ማጠናከርና አሰፈላጊ ግብዓቶች ማሟላት፣የተጎዱ ማህበረሰብ አከባቢዎችን በጤና፣ትምህርትና በንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ ማድረግ እንዲሁም ምግብና ስርዓተ ምግብ ችግሮች ለመቅረፍ ብሎም ቤተሰብ ኑሮ ማሻሻያ ተግባራት የማጠናከር ስራዎች የቀጣዩ አምስት ዓመታት የስራ አካል እንዲሆኑ ከውይይቱ ባለድርሻ አካላት ጋር በመግባባት ውይይቱ ተጠቃሏል።
በፍቅር ከበደ
