



መንግስት የባህል ዘርፉ እንዲጠበቅና እንዲጠናከር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ገለጹ።
በኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ የተዘጋጀ የ72ኛው የቦረና ገዳ ሥርዓት የባሊ ርክክብን በተመለከተ የፓናል ውይይት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩም የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፣ የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምቢሩ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብዱላዚዝ ዳውድ፣ አባገዳዎች፣ ሀዳሲንቄዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በዚሁ ወቅት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ ሚኒስቴሩ የሀገሪቱ ባህልና እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
የገዳ ሥርዓት ተጠብቆ እንዲቆይ የኦሮሞ አባገዳዎችና አባቶች ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና እንደሚገባቸው የገለጹት ሚኒስትሯ፤ መንግስት የባህል ዘርፉ እንዲጠበቅና እንዲጠናከር በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ጀሚላ ሲምቢሩ በበኩላቸው የገዳ ሥርዓት ዲሞክራሲያዊ የአስተዳደር ሥርዓትን ለዓለም ያበረከተ ባህል ነው።
የክልሉን ባህል የማስተዋወቅ እና እሴታቸው ተጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፍ የማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ የገዳ ሥርዓት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ዲሞክራሲዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር የሚደረግበት መሆኑንም ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት የገዳ ሥርዓት በትምህርት ቤት እንደ አንድ ትምህርት እየተሰጠ መሆኑን ገልጸው፤ ልጆች በትምህርት ቤት የዲሞክራሲ ስርዓት ልምምድን እንዲያዳብሩና ባህላቸውን እንዲያውቁ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አብዱላዚዝ ዳውድ ገዳ የኦሮሞ ሕዝብ የፖለቲካ፣ የአስተዳደርና የማህበራዊ ሥርዓት ነው ብለዋል።
ይህ ሥርዓት ለትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ምሁራን በጥናትና ምርምር ሊያግዙ ይገባልም ብለዋል።
የገዳ ሥርዓት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ የዓለም ቅርስ ነው ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
