



የቡና ውጤታማ የግብይት ሥርዓትንና ተጠቃሚነትን ይበልጥ እንዲጎለብት ድጋፉን እንደሚያጠናከር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማኅበር አስታወቀ።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቡና አዘጋጅና አቅራቢ ማኅበር መደበኛ ጉባኤ የፌዴራል እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በሚዛን አማን ከተማ እየተካሔደ ነው።
በጉባኤው የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማኅበር ፕሬዚዳንት ሁሴን አምቦ(ዶ/ር) እንዳመለከቱት፤ የቡና ክፍለ ኢኮኖሚ ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ የምትታወቅበትና የምትወዳደርበት ትልቅ ዘርፍ ነው።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በዘርፉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውን አውስተው፤ ይህ ወጤት ቡና ከማዘጋጀት እስከ መላክ ያሉ የዘርፉ ተዋንያን የትብብርና በጋራ ተናቦ የመሥራት ስኬት እንደሆነ ተናግረዋል።
በተያዘው በጀት ዓመትም የቡና ውጤታማ የግብይት ሥርዓትንና ተጠቃሚነትን ይበልጥ ለማጎልበት ማህበሩ ድጋፉን እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል።
የቡና ምርምር ውጤቶችን ወደ ማሳ በማውረድ የምርታማነትና ጥራት ደረጃ ከፍ እንዲል ከሚመለከተው አካል ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንደሚጠበቅም ጠቁመዋል።
በተለይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ለቡና ልማት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም የልማትና ምርት ምጣኔን ከጥራት ጋር ከፍ በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ቡና ለማቅረብ ማኅበሩ ይደግፋል ብለዋል።
የክልሉ ቡና አዘጋጅና አቅራቢ ማኅበር ፕሬዝዳንት ዝናቡ አባመጫ በበኩላቸው፤ የክልሉን ቡና ውጤታማ በሆነ መንገድ ለማገበያየት አዘጋጆችና አቅራቢ ነጋዴዎች ጋር ተናበን እየሠሩ እንደሚገኙ አብራርተዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ መስፍን መንገሻ፤ ባለፉት ዓመታት የለውጡ መንግስት ለቡና ልማት በሰጠው ትኩረት የዞኑ የቡና ማሳ ሽፋን ከነበረበት 149ሺህ ሄክታር ወደ 160 ሺህ ሄክታር ደርሷል ብለዋል።
ከዚህም ውስጥ ከ135ሺህ ሄክታር የሚበልጠው ማሳ ምርት እንደሚሰጥ ጠቅሰው፤ በ2017 በጀት ዓመት ከ23ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡን አስታውሰዋል።
በመድረኩ በክልሉ የቡና አዘጋጆች፣ ላኪዎችና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።
ኢዜአ
