








ሁሉን አስተሳሳሪ ገዥ ትርክት በመገንባት ጠንካራና የበለፀገች ኢትዮጵያን አውን ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
ህብረብሔራዊ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ለዘላቂ ሠለምና ሁለንተናዊ ብልፅግና በሚል መሪ ሀሳብ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በሚዛን አማን ከተማ ህዝባዊ ዉይይት ተካሂዷል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት የመድረኩ ዓላማ ህዝቡ ሀገራዊ፣ክልላዊ እና አካባቢያዊ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ሰላማዊ ሁኔታን በመረዳት እስካሁን የተመዘገቡት ሁለንተናዊ ድሎች ፀንተዉ እንዲቀጥሉ ለማስቻል እንደሆነ ገልጸዋል።
ሀገራችን የውስጥና የውጭ ፈተናዎችን ተቋቁማ በለውጥ ጎዳና ወደ ብልፅግና ለመሸጋገር
ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያሉትን እምቅ ሀብትና ጸጋዎችን በአግባቡ በመጠቀምና በማስተዳደር ሀብት የመፍጠር ጉዞን በቁጭት መንፈስ አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ጊዜን በአግባቡ መጠቀም እና የሥራ ባህላችንን
በመቀየርና የኑሮ ውድነትን ለማስተካከል
የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የጀመርነው የለውጥ ጉዞ የኢትዮጵያዊያንን
ማህበራዊ መስተጋብርና ትስስር በአዲስ ሀገራዊ ገዥ ትርክት ለመገንባት ሁሉም የህብረተሰቡ ክፍል ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ለፈተናዎች የማትንበረከክ የቆየ አኩሪ ታሪክ ባለቤት መሆኗን የገለጹት አቶ ጥላሁን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ይሄ ትውልድ ጠንክሮ መስራት መቻል እንዳለበት ገልጸዋል።
ጠንካራ ኢኮኖሚ ያላት ሀገር መገንባት የምንችለው በህዝቦች መካከል አንድ ሆነን ስንቆም ብቻ ነው ብለዋል።
ከኋላ ቀር የፖለቲካ ባህል የመነጩ ዕዳዎችን ወደ ምንዳ ለመቀየር ርብርብ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የገጠማትን ሰብራቶችን ለመሻገር ፓርቲያችን ብልጽግና በልዩ ትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ወቅታዊና ጊዜያዊ ፈተናዎችን በመሻገር ሁለንተናዊ የብልጽግናን ጉዞ እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ በበኩላቸው ኢትዮጵያ የታሪክ እጥፋትን መቀየር የቻለች በአዲስ የለውጥ ጉዞ ላይ ትገኛለች ብለዋል።
ብልጽግና ፓርቲ የሚመረው መንግስት በርካታ ስኬቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ ገልጸው እነዚህን ስኬቶች ለማስቀጠልና ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ተከታታይነት ያለዉ ህዝባዊ የውይይቶች መድረኮች ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሠላም፣በአገልግሎት አሰጣጥ፥ በኑሮ ዉድነትና ሥራ አጥነት ዙሪያ እና በመሠረተ ልማት ዙሪያ ጥያቄዎች ተነስተዉ ዉይይት የተደረገ ሲሆን በመጨረሻም ዉይይቱ ለተነሡ ጥያቄዎች በቂ ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸው ተጠናቋል።
