ለአቶ ደመቀ መኮንን የጀግና ሽልማት ተበረከተላቸው::

Spread the love

የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን የሰቆጣ ቃልኪዳን የጀግና ሽልማት ተበረከተላቸው።

አቶ ደመቀ መኮንን ይህን የጀግና ሽልማት ያገኙት ከ37ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ጎን ለጎን በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል እየተካሄደ ባለው የሥርዓተ ምግብ ከፍተኛ መድረክ ላይ ነው።

ለሽልማቱ ያበቃቸውም ለሰቆጣ ቃልኪዳን እውን መሆንና ገቢራዊነት ላደረጉት ጥረትና ቁርጥ የአመራር ብቃት ነው ተብሏል።

በተለይ ደግሞ የሰቆጣ ቃልኪዳን ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 15 ዓመታት ፕሮግራሙ እንዲሳካ ያደረጉት የፖለቲካ አመራር ለሽልማቱ አብቅቷቸዋል ተብሏል።

አቶ ደመቀ የእውቅና ሽልማቱን ከተረከቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፥ አሁንም ድረስ የመቀንጨርና ሌሎችም ከሥርአተ ምግብ ጋር የተያያዙ ችግሮች በመኖራቸው፤ የሰቆጣ ቃልኪዳንን በተጨማሪ ወረዳዎች ማስፋት ያስፈልጋል ብለዋል።

ለዚህም የልማት አጋሮችና የግሉ ሴክተር ትብብር ወሳኝ ነው ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

ከአቶ ደመቀ መኮንን በተጨማሪ ለወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው፣ ለዶ/ር ተከስተ አድማሱ እና ለዶክተር ሊያ ታደስ በየደረጃው ለሰቆጣ ቃልኪዳን እውን መሆን ላደረጉት ጥረት ተመሳሳይ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *