

የአፍሪካ መሪዎች ሙስናን መከላከልና መቆጣጠር ላይ ጠንካራ የጋራ አቋም ሊይዙ እንደሚገባ የአፍሪካ ህብረት የሙስና መከላከል አማካሪ ቦርድ ገለጸ።
የአፍሪካ ህብረት የሙስና መከላከል አማካሪ ቦርድ የስራ አመራሮች ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
የቦርዱ ሊቀመንበር ሴናቡ ዲካቴ፤ ህብረቱ እ.አ.አ በ2003 ሙስናን ለመዋጋት ያወጣው ስምምነት በአግባቡ ተግባራዊ ባለመደረጉ የሚፈለገው ውጤት አለመምጣቱን አንስተዋል።
ቦርዱ የአፍሪካ ህብረት ሙስናን መከላከልና መቆጣጠር ያስችላል ብሎ ያወጣውን ስምምነት አባል ሀገራት ፈርመው እንዲያጸድቁ ግፊት እያደረገ ነው ብለዋል።
ስምምነቱን ተቀብለው ያልፈረሙ ስድስት የህብረቱ አባል ሀገራት መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ሀገራቱን ለማስፈረምና ወደ ትግባራ እንዲገቡ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካ መሪዎች በአህጉሪቱ ትልቅ ፈተና የሆነውን ሙስና ለመከላከል በቁርጠኝነት ሊሰሩ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የቦርዱ ዋና ፀሐፊ ቻሪቲ ቺሙኒ በበኩላቸው ሙስናን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በህብረቱ አባል ሀገራት የወጣው ስምምነት 20 ዓመቱን የደፈነ ቢሆንም የሚፈለገው ውጤት አለመምጣቱን አንስተዋል።
ይህም በአህጉሪቱ የሚፈለገው መሰረተ ልማት እንዳይሟላ ከማድረግ ባለፈ ተጠያቂነት እንዳይሰፍንም አድርጓል ነው ያሉት።
በመሆኑም ህብረቱ ለፀረ ሙስና ትግሉ ያወጣቸው ህጎችና ስምምነቶች ተግባራዊ እንዲሆኑና የተጠያቂነት አሰራር እንዲሰፍን የመሪዎቹ ቁርጠኝነት ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በመሰረተ ልማት የተሳሰረችና የበለፀገች አፍሪካ እውን የምትሆነው አህጉሪቱ ያላትን ሀብት ለሚፈለገው ዓላማ እንዲውል በማድረግ ነውም ብለዋል።
በተለይም የዜጎችን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት እያንዳንዱ ሀገር በሙስና መከላከል ላይ ጠንካራ አቋም ሊይዝ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሙስናን የመከላከል ስራ በአንድ ተቋም ብቻ ሊሰራ የማይችል በመሆኑ በተለይም ዜጎች ሙስናን በማጋለጥ የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው 44ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብስባ ተጠናቋል።
37ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ቅዳሜና እሁድ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ይካሄዳል።
ከትናንት ምሽት ጀምሮ በጉባኤው ለመታደም የተለያዩ ሀገራት መሪዎችና የዓለም አቀፍ ተቋማት ተወካዮች አዲስ አበባ እየገቡ ይገኛሉ ሲል ኢዜአ ዘግቧል።
