
በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው ለመልካም አስተዳደር ችግር መፈጠር መንስኤ የሚሆኑ አካላትን የማጥራት ሥራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን በስብሰባው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የምክር ቤት አባላቱ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊያና ፖለቲካዊ መስኮች እንዲሁም ወቅታዊ ጥያቄዎችን የተመለከቱ ያቀረቡ ሲሆን ከእነዚህ መካከልም በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሆነው የመልካም አስተዳደር ችግር የሚፈጥሩ አካላት ጉዳይ ይገኝበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ አገልጋዮች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ ግንዛቤ የመፍጠርና አቅም የመገንባት ሥራዎች ላይ ትኩረት ተደርጓል ብለዋል።
እንዲያም ሆኖ ከሕግ ውጭ የሚንቀሳቀሱ ሕገ-ወጦች መኖራቸውን አስታውሰው ይሄንን የማጥራት ጉዳይ እንደሚቀጥል አብራርተዋል።
ለአብነትም በ2016 ዓ.ም ባለፉት ስድስት ወራት በየደረጃው ካሉ አመራሮች ውስጥ 8 በመቶ ያህሉ ላይ እርምጃዎች መወሰዱን ገልጸዋል።
በዚህም ከ4 በመቶ በላይ አመራር ከሥራ እንዲሰናበቱ የተደረገ ሲሆን ከ4 በመቶ በላይ ደግሞ ከደረጃ ዝቅ እንዲሉ መደረጉን ነው የተናገሩት።
